በሽግግር ፍትሕ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር መድረክ ሴክሬታሪያት እና በጀስቲስ ፎር ኦል የጋራ ጥምረት የተዘጋጀና በኢትዯጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲና ቀጣይ በሚኖሩ ተግባራት ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከተለያዩ ተቋማት ለተወከሉ የሕግ ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡
ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዳሬክቶሬት እና ከመከላከያ ሚኒስቴር የሕግ ዳሬክቶሬት የተወከሉ ከ40 በላይ የሕግ ባለሙያዎች የተሳተፉበትን ሥልጠና የሰጡት የሽግግር ፍትሕ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር መድረክ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ካሳ ባደረጉት ገለፃ፤ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዓላማ ሀገሪቱ በምትገኝበት አውዶች ላይ ተመስርቶ የተቀናጀ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት እና የሚተገበርበትን ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ የሚረጋገጥበትን መደላድል መፍጠር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የፖሊሲ አማካሪው አያይዘውም የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነትን ሲያስረዱ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥት መዋቅሮች፣ በግለሰቦችና ተቋማዊ ተዋንያን የተፈጸሙ ግጭቶች፣ በደሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መደጋገማቸው በዘላቂ ሰላም ግንባታውና፣ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፈጠሩ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ለረጅም ዘመናት ለተፈፀሙ በደሎች ፍትሕን ለማስገኝት፣ ቁርሾዎችን ለመቀነስና ግጭቶችን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እስከ መጨረሻው አስቁሞ ተጠያቂነትን በማስፈን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ የፖሊሲውን መውጣት አስፈላጊ እንዳደረገው ተናግረዋል፤ አክለውም የወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነት ማፈላለግ፣ ምሕረት፣ ማካካሻ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች በሚሉ አበይት መሰረቶች ላይ የትኩረት አቅጣጨው አድርጎ የተዘጋጀውን ፖሊሲ ህብረተሰቡን አሳምኖና አስተባብሮ በአንድ አስተሳሰብ የሽግግር ፍትሕ ስርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች ያላቸው ሚና ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በተያዘው መርሀ-ግብር መሠረት በሀገሪቱ የፍትሕ ስርዓት ላይ ዜጎች ቁርጠኛ የሆነ እምነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚረዱ ሳይንሳዊ መርሆችን በማስመልከት ሥልጠና የሰጡት ስዊድን ሀገር በሚገኘው ሉንድ ዩኒቨርስቲ የጥናት ባለሙያ፣ ጠበቃና አደራዳሪ የሆኑት ዶ/ር ራስመስ ዋንዳል ባደረጉት ገለፃ፤ ለሽግግር ፍትሕ ስኬታማነት በስርዓቱ ላይ ሙሉ እምነትን ማሳደር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በርካታ የአለም ሀገራት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩትን አይነት ችግሮች በሽግግር ፍትሕ ስርዓት ተረድተው ማለፋቸውን አስታውሰው፤ ህብረተሰቡ ሂደቱ የራሱ የሆነ ጊዜን የሚፈልግ መሆኑን ተገንዝቦ ይህ ጉዳይ እኔንም ይመለከተኛል የሚል አስተሳሰብን በመያዝ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ቀጥሎ የቀረበውን የሽግግር ፍትሕ እና የልዩ ፍርድ ቤቶችን አሠራር በማስመልከት የተዘጋጀውን ሥልጠና የሰጡት ከኦስትሪያ ቬና ዩኒቨርስቲ የመጡት ተመራማሪና የዓለም ዓቀፍ ወንጀል ሕግ ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ኦስትሪድ ፋይዚንገር ነፃ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው የሚሰሩበትን መርሆች አስረድተው፤ የሽግግር ፍትሕ በአርጀንቲና፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በላይቤሪያ እና በሌሎች በርካታ ሀገራት ተግባራዊ ተደርጎ ስኬታማ መሆኑን አውስተዋል፡፡ አያይዘውም በኢትዮጵያም ውስጥ የተዘጋጀውን ፖሊሲ መሠረት አድርጎ መሥራት ከተቻለ የሚፈለገው ውጤት መድረስ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ዙሪያ ተሳታፊ በነበሩት ሰልጣኞች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ታላቅ ሀገራዊ አጀንዳን የያዘ ሁሉም ዜጎች በንቃት ተሳትፎ አድርገው ያለፉትን እና ወቅታዊ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችንን በመቅረፍ ፍትሕና ሰላም የሰፈነባት ሀገርን ለመገንባት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ መሆኑን መገንዘባቸውን እና ለተግባራዊነቱም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡