በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚንስቴር በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በሐረሪ ክልል ለሚገኙ የፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ፖሊስ አባላት በወንጀል መከላከል እስትራቴጂ እና በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ ከታህሳስ 14 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ .ም ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና በሀረር ከተማ መስጠት ተጀምሯል፡፡
ሥልጠናው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ምክትል ሀላፊ የሆኑት አቶ ለታ በዳዳ እንደገለፁት የፓሊስ ትልቁ ስራው ወንጀልን መከላከል ነው ወንጀል ደግሞ በባህሪው እየዘመነ ነው አንዳንድ ጊዜ ወንጀልን ለመከላከል ብለን ሰብዓዊ መብቶችን እንዳንጥስ ፓሊስ በረቀቀ እና በፖሊሳዊ ሳይንስ ወንጀልን መከላከል ይኖርበታል። በዋናነት ይህ ሥልጠና የወንጀል መከላከልን ስንሰራ እራሳችንን ለማብቃት ትምህርቱ አቅም ይሰጠናል ብለዋል።
ሀላፊው አክለውም ይህ ሥልጠና ለወንጀል መከላከል ፖሊስ አባላት የሚሰጠው የሰልጣኞችን አቅም ለማጎልበት አስፈላጊ በመሆኑ የሥልጠና ዲስፕሊን በመጠበቅ በንቃት እንዲሳተፋ አሳስበዋል።
የክልሉ ወንጀል መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳሪክተር የሆኑት ኮ/ር አብዲ ኤብራሄም በበኩላቸው እኛ የሕዝብ አገልጋዮች አሁን ባለው አሁናዊ ሁኔታ እንዴት ነው የዜጎችን መብት በማክበር ሰብዓዊ መብትን ሳንጥስ ወንጀልን መከላከል የምንችለው? ለሚለው ጥያቄ ሰልጣኞች ከሥልጠናው በቂ ምላሽ የሚያገኙበት ነው ያሉት ኮ/ሩ፣ ሰልጣኞች ሰዐት በማክበር እንዲሁም ግልፅ ያልሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት በሥልጠናው ወቅት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በአፅንኦት አሳስበዋል።
ሥልጠናው በኢ.ፌ. ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ም/ረ/ጠ/ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ግርማ እና ረ/ጠ/ዐቃቤ ሕግ አቶ ተክለ ልብሰወርቅ የሚስጥ መሆኑ ተጠቅሷል።