በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መሠረታዊ ወንጀል ምርመራ ሂደት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሥልጠና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለተዉጣጡ የሴቶችና ሕፃናት ወንጀል መርማሪዎች በቢሾፍቱ ከተማ በመሰጠት ላይ ነዉ፡፡
ሥልጠናዉ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ተከተሎ የሚከናወኑ የምርመራ እና የክርክር ሂቶችን በተሻለ መልኩ ለመምራት እንዲያግዝ ታስቦ መዘጋጀቱን በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች ሕፃናትና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ ተናግረዋል፡፡
አያይዘዉም እነዚህ ወንጀሎች በባህሪያቸዉ ልዩ እና ዉስብስብ ከመሆናቸዉ አንጻር በዘርፉ የተሰማሩ መርማሪዎችን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግና በጋራ ልምዶችን በመለዋወጥ የምርመራ ስርአቱን ለማገዝ የሚያስችሉ አካሄዶችን እየፈጠሩ መሄድ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የሰዉ መግደል ምርመራ ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ በበኩላቸዉ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ጋር በተገናኘ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዉ ወንጀሉ የሚፈፀምባቸዉ ሴቶችና ሕፃናት የሚፈፀምባቸዉን ወንጀል ለመቋቋም አቅም የሌላቸዉ መሆናቸዉን ተገንዝቦ አሰራሩን በማጠናከር የምርመራ ስራዉን በትኩረት ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አክለዉም በተለይም የቅድመ መከላከል ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዉ ወንጀል ሲፈፀምም በአግባቡ አጣርቶ እና መርምሮ ለሚመለከተዉ ባለድርሻ አካል ማስተላለፍ በምርመራ ከተሰማሩ ፖሊሶች የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሥልጠናዉም መሠረታዊ የወንጀል ምርመራ እና የወንጀል ስፍራ ማስረጃዎች በሚሉ ይዘቶች ላይ ተመስርቶ እየተሰጠ ሲሆን የወንጀል ምርመራ ትርጉም፣ዓላማ እና አይነት፣የወንጀል ምርመራ ደኅንነት፣ የወንጀል ስፍራ ማስረጃ አይነቶች፣ ማስረጃ አሰባሰብ፣ አያያዝና አላላክ፣ በወንጀል ስፍራ የመርማሪዎች ሚና የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተዳሰዉበታል፡፡