በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር አካታች የሆነ የስርአተ ጾታ ሕግ እና መደበኛ የሕግ አረቃቀቅ ክህሎት ማዳበር ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከክልል እና ከፌዴራል ተቋማት ለተወጣጡ የሕግ ማርቀቅ ባለሙያዎችና አመራሮች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ፣ማርቀቅና ማጠቃለል ምክትል ኃላፊ ቃልኪዳን ደረጀ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው ፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል መንግሥት የሕግ አማካሪ የሆነና ፣የፌዴራል ህጎችን የማርቀቅ ፣ተረቀው የሚመጡ ህጎችን የማረም እና የማስተካከል ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሕግ ማርቀቅ የፖሊሲ አቅጣጫን ወደ ሕግ ማዕቀፍ መቀየር መሆኑን ያወሱት ምክትል ኃላፊዋ ፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ ማርቀቅ እና በተለያዩ ህጋዊ ጉዳዮች ላይ የክልል አካላትን የመደገፍ ተግባርና ኃላፊነትን ይዞ የሚሰራ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በሕግ አረቃቀቅ ላይ የባለሙያዎችን ክህሎት ማዳበርና ማብቃት አንዱ የተቋሙ ተግባርና ኃላፊነት በመሆኑ በእቅድም ተካትቶ እየተሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያረቃቸው ህጎች ጥራታቸውን የጠበቁ፣ወጥነት ያላቸው ፣ተደራሽ የሆኑ እንዲሁም ለአስፈፃሚውና ፈፃሚው አካል ብቃት ያለው እና ውጤታማ የሆነ የሕግ አረቃቀቅን የሚከተሉበት መመሪያና ማኑዋል መኖሩን አክለው ጠቁመዋል፡፡
ሥልጠናው የሕግ አረቃቀቅ ፅንሰ ሀሳቦችን ፣መርሆዎችን ፣የቃላት አጠቃቀም፣መዋቅር ፣ይዘት እና አካታችነት በሚሉ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ያወሱት ቃልኪዳን በፖሊሲዎቻችንና በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ እና ሌሎች የሴቶች መብቶች እንዲከበሩ የማድረግ ግዴታን አካትቷል ብለዋል፡፡
ምክትል ኃላፊዋ ስርዓተ ጾታን ያማከለ ሕግ መቅረፅ የሚቻለው እንዴት ነው የሚለውን ማኑዋል መሠረት በማድረግ እና በጥናቱ የተነሱትን ክፍተቶች በመለየት ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
የፕሪሳይስ አማካሪ ፕሮጀክት አስተባባሪ ምሕረት ታምር በገለጻቸው በ2014 ዓ.ም ስርዓተ ጾታን ያማከለ የሕግ አረቃቀቅ ጋይድ ላይን ፀድቆ ተግባር ላይ መዋሉን አውስተው የጋይድ ላይኑ አተገባበር ምን ይመስላል የሚል ምዘና በዚህ ዓመት መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
አስተባባሪዋ አያይዘውም በጥናቱ መልካም የሆኑና መሻሻል የሚገባቸው ሁኔታዎችን ለማወቅ በሲዳማ ፣በሱማሌ፣በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ላይ በተደረጉ ቃለመጠይቆች መረጃዎችን ማሰባሰብ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ሥልጠናው በሕግ ማርቀቅ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩ በሙያው የዳበረ ልምድ ያላቸው በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ፣ማርቀቅና ማጠቃለል ጄኔራል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲስ ጌትነትና ሐመልማል በቀለ የተሰጠ ሲሆን ሥልጠናውን ፍትሕ ሚኒስቴር ከPRECISE COUNSELT ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነው፡፡