ኢትዮጵያ አገራችን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ የማደግ፣ የመልማት እና የመበልጸግ ትልሞችን እውን ለማድረግ እና የዜጎችን ክብርና ጥቅም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር፣ የሌማት ትሩፋት እና የስንዴ ልማት አጀንዳዎች ላይ በመንግሥት መሪነት ሕዝብን ያሳተፈ በሁሉዓቀፍ ርብርብ በማድረግ የቅቡልነት ማህተም የሆኑ ለውጦችን እውን ማድረግ ተችሏል፡፡
በዘንድሮ በጀት ዓመትም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ያስጀመሩት የክረምት የበጎ አድራጎትና የአረንጓዴ አሻራ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፍትሕ፣ የመከላከያ እና የሰላም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ተጠሪ ተቋሞች በጋራ በመሆን እያካሄዱት ያለው የክረምት የበጎ አድራጎት እና የአረንጓዴ አሻራ ሥራ መርሃ ግብር እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ መርሃ ግብር በኦሮሚያ ክልል ሎሜ ወረዳ የተጀመረ ሲሆን ቀጥሎ በዛሬው እለትም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማረቆ ልዩ ወረዳ እና በጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ልዩ ወረዳዎች በመገኘት የአገር በቀል ችግኝ እና ፍራፍሬ በመትከል የአረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችና ት/ቤት እድሳት እና የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን አከናውነዋል።
በዚህ የበጎ ሥራ አሻራ ማሳረፊያ መርሃ ግብር ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ ጨምሮ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ፣ የዞን እና የወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎች ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ የማረቆ ልዩ ወረዳ ላደረገው አቀባበል ምስጋና አቅርበው በየዓመቱ እየተካሄደ ባለው የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ መርሃግብር መሠረት በዘንድሮው ዓመትም የተለያዩ በጎ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀው በዚህ በማረቆ ልዩ ወረዳም ሦስት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዚሁ መሠረትም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በሚመለከት በእጆቻችን እየሰራን አንደ ምልክት ሆኖ የሚቀጥል ስራ በማስቀመጥ የአገራችን ልማት ማረጋገጥ ይኖርብናል ያሉት ክብርት ሚኒስትር በተጨማሪም ወቅታዊ ስራዎች ላይ ከማተኮር በዘለለ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ሥራን በመሥራት ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም በጥቅሉ እድገትና ልማት ሲታሰብ አካታችና ሁሉንም ሰው ያቀፈ መሆን እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተው የአቅመ ደካማ ቤቶችን እና ትምህርት ቤቶችን ማደስና መገንባትም ሌላኛው የበጎ ሥራ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።
ሰላምና ፍትሕን ለማስፈን በትኩረት እየተሥራ መሆኑን የገለፁት ክብርት ሚኒስትሯ በአካባቢው ያሉ ትልቅ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ሕጋዊ እውቅና በመስጠት ለመደበኛው የፍትሕ ሥርአት አጋዥ እንዲሆኑ በማስቻል ባህላዊ የፍትሕ ሥርአቶችን በቁርጠኝነት መተግበር እንደሚገባ አመላክተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው የሰላምና የፍትሕ አካላት ወደ ልዩ ዞኑ የችግኝ ተከላና ሌሎች የክረምት በጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመከወን ስለተገኙ ምስጋና አቅርበው አካባቢው ከግጭት ወጥቶ ሰላም የተረጋገጠበት መሆኑ አንዱ ማሳያ የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር መሆኑን አንስተዋል፤ ሰላም የሁሉም መሠረት መሆኑንም አክለዋል።
በተያያዘም በሰላም እና ደኅንነት ዙሪያ ከአካባቢው ወጣቶች ጋር አጠር ያለ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በዚህ ወቅት የፍትሕ ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ ወጣቶች በተሰማሩበት የሥራ መስክ በከፍተኛ ጀግንነት በመሥራት ለሀገራቸው ልማት፣ሰላም እና ብልፅግና ብሎም የሀገራቸውን ሉአላዊነት መከበር ሊተጉ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በጥቅሉ በዘንድሮው የክረምት መርሃግብር በፍትሕ፤ በመከላከያ እና በሰላም ሚኒስቴር መ/ቤቶች እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት በጥምር የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት፣በአረንጓዴ አሻራ፣በደም ልገሳ፣የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በዚህም በጥቅሉ በኦሮሚያ ክልል ሎሜ ወረዳ፣ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምስራቅ መስቃን ወረዳ እና ማረቆ ልዩ ወረዳዎች 35 ቤቶች፣ 55ሺህ ችግኞች እንዲሁም ለ3000 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡