"ትውልዱ ለችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦች የሚያመነጭ እና በውይይት የሚያምን ሊሆን ይገባል" -ኘሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ

"The Generation Should be Solution-Oriented and Believe in Dialogue" - President Sahle-Work Zewde

ትውልዱ ለችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦች የሚያመነጭ እና በውይይት የሚያምን ሊሆን እንደሚገባል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኘሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ይህ የተገለጸው የትውልድ ቀን “ኢትዮጵያ የትውልድ ድምር” በሚል መሪ ሃሳብ በፓናል ውይይት በተከበረበት ወቅት ነው።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኘሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባስተላለፉት መልዕክት ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት በመልካምም በመጥፎም የሚታወሱ ትውልዶችን አፍርታለች ብለዋል።

ሀገር የምትገነባው በትውልዶች ቅብብሎሽ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ ትውልዱ ለችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦች የሚያመነጭ እና በውይይት የሚያምን ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።

አክለውም ሀገር ወዳድነት፣ ሀቀኝነት፣ አገልጋይነት ያሉ መሠረታዊ ዕሴቶች ሊጠበቁ ይገባል ያሉ ሲሆን ትውልዱ ማንበብ፣ መመራመር እና መጠየቅ ይገባዋል ብለዋል።

በትውልዶች መካከል የልምድ ልውውጥ ሽግግር ባህል ማጎልበት ይገባል፤ ያለፍንባቸውን መንገዶች እየመረመርን መጓዝ፣ በአግባቡ በትምህርት የታነጸ ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።

ለዚህም ከቤተሰብ ጀምሮ ማኅበረሰብ ላይ መሥራት ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፣ ትውልዱ በአግባቡ የተማረ፣ ተወዳዳሪና አገሩን የሚወድ ሊሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ትውልዱ ካለፈው ትውልድ አገር መውደድን በመማር ያለፈውን ትውልድ ስህተት ባለመድገም መሆን አለበት ብለዋል።

የተሟላና መልካም ስብዕና ያለው ትውልድ ለሀገር እድገት ጉልህ ፉይዳ ስላለው የግብረ ገብነት ትምህርት በአዲሱ ስርዓተ – ትምህርት ውስጥ እንዲካተት መደረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ትምህርት ቤቶች የዚህን ትውልድ ግብረ ገብነት የማሻሻል ኃላፊነት አለባቸው ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልጸዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የዕድገትና የበጎነት እንዲሆን ተመኝተዋል።

በዕለቱ የትውልዶች ቅብብሎሽና ሽግግር ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የዘንድሮ የትውልድ ቀን በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን በበዓሉ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኘሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ታዳጊ ህጻናት እና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

Relevant Departments and People
Tagged Under: civic civic education development dialogue Education education reform Experience Sharing intergenerational moral moral values National National Development national identity National Unity sahle-work sahle-work zewde unity values youth youth development youth engagement zewde
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች