የአስፈጻሚ ተቋማት የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅን በተሻለ በመፈጸም የሕዝቡን አስተዳደራዊ ፍትሕ ጥያቄ በሚመልስ መልኩ መፈጸም እንዲችሉ በአዋጁ ዓላማ እና ይዘት ዙሪያ ለተለያዩ ተቋማት አመራሮች ሥልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል። በዚህም መሠረት ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ለስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
የሥልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል ፍትሕ ሚኒስቴር በቅርበት አብረው ከሚሰሩት ተቋም መካከል ዋናው መሆኑን አንስተው ስለአዋጁ ጠቀሜታ ሲገልጹ ሥልጠናው አዋጁን በደንብ ባለማወቅ የሚፈጠሩ ስህተቶችን በማረም በውሣኔ አሰጣጥና መመሪያ አወጣጥ ሂደት ለሕጉ በመገዛት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ያግዛል ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ እና እገዛም አመስገነዋል፡፡
በአዋጁ በተዳሰሱ ጉዳዮች ስለ መመሪያ አወጣጥ ሂደትና ስለ አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ፣ በአዋጁ የተቀመጡትን ግዴታዎች አለማክበር የሚያስከትለውን ውጤት እና በፍርድ ቤቶች ኃላፊነትና ሥልጣን ዙሪያ እንዲሁም የአዋጁ መተግበር ያለው አጠቃላይ ፋይዳ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በአዋጁ አተገባበር ላይ ለታዩ ክፍተቶች ዋና ምክንያት ሆኖ የተለየውን የተቋማት የግንዛቤ ክፍተት ለመቅርፍ እንዲሁም ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሩን ለማብቃት የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ገለፃውን ተከትሎ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አሰግድ ጌታቸው ከተሳታፊዎች የተነሱትን ጥያቄዎች ያሳለጡ ሲሆን፣ ለተነሱት ጥያቄዎች ከባለሙያዎች ምላሽ ተሰጠቶባቸዋል፡፡
መርሀ-ግብሩን ሚኒስትር ዴኤታው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የሚሰራውን ስራ ከአዋጁ አንፃር መፈተሽና ማስኬድ እንደሚገባ አሳስበው ለአዋጁ አተገባበር በቀጣይ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኛና በዛሬው ሥልጠና መገኘት ያልቻሉ አመራሮች በተገኙበት ሊሰጥ የሚገባ መሆኑንና ለዚህም ፍትሕ ሚኒስቴር ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠቁመዋል፡፡