በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጉዳይ መከታተያ ዳይሬክቶሬት ስር የሚመሩ ጽ/ቤቶች በ2015 በጀት ዓመት ያከናወኗቸው ተግባራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊዎች በተገኙበት የተካሄደውን የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የውይይት መድረክ የመሩት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጉዳይ መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ መድረኩ በ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም የተገኙ ጠንካራ ጎኖች ጎልብተው የሚቀጥሉበትን እንዲሁም የታዩ ክፍተቶች የሚስተካከሉበትን አቅጣጫ የሚያመላክት መሆኑን አስታውሰው፤ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙትን የ10 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዲሁም የድሬ ዳዋ እና ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የእቅድ አፈፃፀም ዝርዝር ገለፃ አድርገዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት መሠረትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የወንጀል ሕግ አፈፃፀም ውጤታማነትን በማሳደግ ረገድ ምርመራቸው ተጠናቆ ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ለውሳኔ ቀርበው መወሰን ያለባቸውን 32,006 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 80% ያህሉን ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ በ30,265 ወይም 94.56% መዝገቦች ላይ ውሳኔ በመስጠት ከእቅዱ አንፃር የ14.56% ብልጫ በማከናወን መፈፀሙ ተጠቅሷል፡፡
የወንጀል ክሶችን የመርታት ምጣኔ አፈጻጸምን በሚያመለክተው የሪፖርቱ ክፍል ላይ እንደተመከተው በመደበኛ መዛግብት የመርታት ምጣኔን በተከሳሽ 90% በመዝገብ ደግሞ 94.5% ለማድረስ ታቅዶ በክርክር ላይ ከነበሩ 29,806 መዛግብት እና 38,995 ተከሳሾች ውስጥ ፍርድ ቤት በ12,440 መዛግብት እና በ14,540 ተከሳሾች ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ በ12,084 መዛግብት እና በ14,091 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት፣ እንዲሁም በ356 መዛግብት እና በ449 ተከሳሾች ላይ ነፃ በማለት ፍርድ የሰጠ በመሆኑ አፈፃፀሙም በመዝገብ 97.14% በተከሳሽ ደግሞ 96.91% ሲሆን በአማካይ አፈፃፀሙ 97.03% በመሆኑ ከዕቅድ በላይ መፈፀሙን በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል፡፡
በቀረበው የ2015 በጀት ዓመት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ክርክር ላይ ከነበሩ 30,509 መዛግብት ውስጥ 1,549 መዛግብት ምስክሮች ባለመቅረባቸው ተቋርጠዋል፡፡
በፍርድ ቤት ከሚሰጡ የገንዘብና የእስራት ቅጣቶችን የማስፈፀም ተግባርን በሚመለከትም በ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ መጠኑ ብር 14,369,432 (አስራ አራት ሚልዮን ሶስት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺህ አራት መቶ ሰላሳ ሁለት ብር) የሆነ የገንዘብ መቀጮ በተከሳሾች ላይ ተወስኖባቸው ከዚህም ውስጥ መጠኑ ብር 9,910,348.2 (ዘጠኝ ሚልዮን ዘጠኝ መቶ አስር ሺህ ሶስት መቶ አርባ ስምንት ብር ከሁለት ሳንቲም) ወይም 68.97% ክትትል በማድረግ ማስፈፀም መቻሉ፤ በሌላም በኩል በፍትሀ ብሔር ጉዳዮች የመርታት ምጣኔን በተመለከተም የፍትሐ ብሄር ቀጥታ ክስ ክርክር መዛግብት የመርታት ምጣኔ፤ በክርክር ላይ ካሉ 326 የቀጥታ ክስ ውስጥ ፍርድ ቤት በ155 መዛግብት ላይ ውሳኔ ሲሰጥ በ151 መዛግብት ላይ ዐቃቤ ሕግ በመርታት አፈፃፀሙን 97.42% ማድረስ መቻሉን፤ እንዲሁም በፍትሐ ብሔር የይግባኝ ክርክር መዛግብት የመርታት ምጣኔ በክርክር ላይ ከነበሩት 47 መዛግት ውስጥ ፍርድ ቤት በ31 መዛግብት ላይ ውሳኔ ሲሰጥ በ29 መዛግብት ላይ ዐቃቤ ሕግ በመርታት አፈፃፀሙን 93.55% በማድረስ ከዕቅድ በላይ በመፈፀም በሁለቱ አማካይ አፈፃፀሙ 95.5% መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትን ከማሳደግ አንፃር በበጀት አመቱ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና ሌሎች ግለሰቦች የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት ጠበቃ ቀጥረው የሕግ ምክር አገልግሎት እና መከራከር ያልቻሉ 1,720 በላይ ባለጉዳዮችን የፍትሐብሄር ዐቃብያነ ሕግ እንዲይዙላቸው በማድረግ ከ34,517,498 (ከሰላሳ አራት ሚልዮን አምስት መቶ አስራ ሰባት ሺህ አራት መቶ ዘጠና ስምንት ብር) በላይ የያዘ የዜጎች መብት በነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት እንዲጠበቅ ማድረግ መቻሉ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡
ሪፖርቱ በዝርዝር ገለፃ ተደርጎበት ከቀረበ በኋላ በተሳታፊዎቹ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የተለያዩ አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በተለይም በዚህም በተገባደደው በጀት ዓመት የተስተዋሉ የሠራተኛ እጥረት እና የመረጃ አያያዝ ክፍተቶች በቀጣዩ የስራ ዘመን ላይ ማስተካከያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ በአፅንኦት የተገለፀ ሲሆን፤ በመጨረሻም በተነሱት አስተያየቶች ላይ ከመድረኩ ማብራሪያ ተሰጥቶ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የ2015 በጀት ዓመት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የእቅድ አፈፃፀም የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡