የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ /TDB Group/ ጋር በመተባበር በዓለምዓቀፍ ውል ዝግጅትና ድርድር ሂደቶች ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስራ ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል፡፡
ከፌዴራል እና ከክልል ተቋማት የተወከሉ በውል ሂደት ለሚሳተፉ ከ56 በላይ የሕግ ባለሙያዎች ከሐምሌ 21 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በሚሰጠው ተግባር ተኮር ሥልጠና ላይ በመስኩ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ዓለምዓቀፍ እና የውጭና ሀገር ውስጥ አሰልጣኞች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ ውሎችን በሚገባ በመደራደርና የተቋማትን ጥቅም በተሟላ ሁኔታ የሚያስጠብቁ ስምምነቶችን በማዘጋጀት የሕዝብና የመንግሥት ጥቅም ለማስጠበቅ አጋዥ የሆነና ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ባለሙያዎች የተሳተፉበት በዓይነቱ ልዩ የሆነ የዓለምዓቀፍ የውል ድርድርና ዝግጅት ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ /TDB Group/ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የ/TDB Group/ ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አድማሱ ታደሰ፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ መስራች አገር መሆኗን አስታውሰው፣ የ/TDB Group/ በተለያዩ አገራት በግብርና እንዲሁም በኢንደስትሪ ዘርፎች ከዚህ በተጨማሪ በቢዝነስ ውልና ድርድሮች ላይ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በመሳተፍ ዓለምዓቀፍ የውል ዝግጅትና ድርድሮች ላይ ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን ላይ የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አንፃር ዓለምዓቀፍ የቢዝነስ ውል ድርድርና ዝግጅት ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎችን ለማብቃት ታሳቢ ተደርጎ ሥልጠና መዘጋጀቱ በዘርፉ ላይ ተጨማሪ አቅምን መፍጠር የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለተከታታየ አምስት ቀናት የሚቆየውና ትኩረቱን ዓለምዓቀፍ የቢዝነስ ውል ዝግጅትና ድርድሮች ላይ ያደረገ የአቅም ግንባታ የሥልጠና መድረክን የመክፈቻ ንግግር በማድረግ በይፋ ያስጀመሩት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሐን{ዶ/ር} ሥልጠናውን በማዘጋጀት የተባበሩ አጋር አካላትን አመስግነው የአቅም ግንባታ ሥልጠናው የፌደራል ተቋማትና ክልሎች የውል ሥራዎቻቸውን በእውቀት የተደገፈ እንዲሆን በማስቻል በአገራችን በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የሕዝብና የመንግሥት ተቋማት በጀትና ሃብቶች ይበልጥ እንዲጠበቁ እንደሚያስችል አልፀዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ክልሎችን ጨምሮ በሁሉም ደረጃ የሚደረገው የአቅም ግንባታ ሥራ የአገርና ተቋምን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ውሎች እንዲመሩ በማድረግ የሕዝብ በጀት እንዲጠበቅና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱን ለመደገፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለው እንደገለጹት የውል ድንጋጌዎችን አስመልክቶ አለመግባባት ከመከሰቱ በፊት በተለይ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በቢሊዮን ብር የሚገመቱ የፕሮጀክት ውሎች ድርድርና ዝግጅቶች በሚገባው የጥንቃቄ ደረጃና በትኩረት መመራት እንዲችል መሰል የተግባር ሥልጠናዎች አጋዥ መሆናቸውን በመጥቀስ ሥልጠናው በዘርፉ የሚስተዋለውን የሙያ አቅም ክፍተቶችን ለመሙላትና አሁናዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሙንና ዓለምዓቀፍ ከባቢ ሁኔታው እድገት የሚፈልገውን ዝግጁነት በማጎልበት የሕዝብን ጥቅም በተሟላ መልኩ ያማከለ ምላሽ ለመስጠት አጋዥ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
በዚህ ሥልጠና የሚገኘው ክህሎት በቀጣይ በሚኖሩ ሥራዎች ላይ አተገባበሩ አፅንኦት ተሰጥቶት ክትትል የሚደረግበት መሆኑና ከመሰል የልማት አጋሮች ጋር በመቀናጀት ተከታታይ ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱ ተመላክቷል፡፡ በዓለምዓቀፍ ውል ዝግጅትና ድርድር ሂደት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ሥራ ሥልጠና ተዘጋጅቶ እንዲሰጥ በተለያየ ደረጃ አስተዋፅኦ ያበረከቱት Trade and development bank group(TDB Group) ፣ African Legal Support Facility (ALSF), New Perimeter እና DLA PIPER ሲሆኑ እስከ ሀምሌ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ መድረክ ዓለምዓቀፍ የቢዝነስ ውል ዝግጅትና ድርድር ቴክኒኮች ዙሪያ ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እንደሚሰጥ ለመረዳት ተችሏል፡፡