የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በፍትሕ ሚኒስቴር የሚሰጡ አገልግሎቶች በብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብቻ እንዲሆኑ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ስለሆነ ተገልጋዮች ይህንን አውቀው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያው በአዋጅ ቁጥር 1284/14 መሠረት ዕውቅና ያገኘ መሆኑን ያሳወቁት ሚኒስትር ዴኤታው እያንዳንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብቻ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት እያንዳንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በስሩ ያሉ ሰራተኞችና ተገልጋዮች አገልግሎቱ ሙሉ ለሙሉ ወደትግበራ ከመግባቱ በፊት ብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት እንዲመዘገቡ እና በእጃቸው እንዲያስገቡ አቅጣጫ መሰጠቱን አመላክተዋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር በሚኒስቴር መ/ቤቱና በተጠሪ ተቋማቱ ስር ላሉ የስራ ክፍሎች እንዲሁም ለጠበቆች ማህበርና ለጠበቆች ቦርድ ከሶስት ወር በፊት በተፃፈ ደብዳቤ መታወቂያውን ለማግኘት መመዝገብ እንዲችሉ ማሳወቁን የገለጹት ሚኒስትር ዴዔታው እያንዳንዱ ሠራተኛና ተገልጋይ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብቻ በመያዝ አገልግሎት እንዲሰጥና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በሚለው የ3 ወር ግምገማ በጋራ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተገምግሞ አቅጣጫ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አገልግሎት የሚያገኙ ጠበቆች እና ሌሌችም የሚመለከታቸው አካላት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብቻ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ ስለሆነ አገልግሎት ፈልገው ወደተቋሙ የሚመጡ ግለሰቦች ለብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ በመመዝገብ የካርድ ህትመትን በመያዝ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አሳውቀዋል፡፡
ለብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያው በተመረጡ ባንኮች ፣በገቢዎች ሚኒስቴር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ስር በሚገኘው የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ፣በዋናው ፖስታ ቤት ፣አራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት መግቢያ ፓላስ ፓርኪንግ ሕንጻ 3ኛ ፎቅ ላይ አገልግሎቱ የሚሰጥ በመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ወደሚያመቻቸው ቦታ በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት እንዳለባቸው ሚኒስትር ዴዔታው አሳስበዋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱን ወደ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ስለሚቀይር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታው በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡