በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት/International Arbitration/ ዙሪያ ተግባር ተኮር ሥልጠና ተሰጠ
ፍትሕ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም /UNDP/ ጋር በመተባር በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ዙሪያ ተግባር ተኮር የሆነ ሥልጠና ለዐቃቤያነ ሕግ ሰጠ፡፡
ሥልጠናው የተሰጠው በፍትሐ ብሄር ፍትሕ አስዳደር ዳይሬክቶት ጄነራል ውስጥ ለሚሰሩ ባለሞያዎች እና በአስሩም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የፍትሐብሄር ስራዎችን ለሚሰሩ እና ለሚያስተባብሩ ባለሞያዎች ሲሆን ከፍትሐ ብሄር የስራ ክፍል ጋር የስራ ግንኙነት ካላቸው ሌሎች የስራ ክፍሎች ባለሞያዎችም በሥልጠናው ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡
ሥልጠናው ፍትሕ ሚኒስቴር በተለይ መንግሥትን እና የመንግሥት ተቋማትን በመወከል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን በዓለም ዓቀፍ መድረክ በሚቀርቡ የግልግል ዳኝነት ክርክሮች ላይ ለሚያደርገው ተሳትፎ ባለሞያዎቹን ብቁ በማድረግ ረገድ አስተዋጾ ያደርጋል፡፡
ሥልጠናውን የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ያስጀመሩት የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ እና ፕሮጀክት ክትትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኖህ ታከለ በንግግራቸው እንደገለጹት ተቋሙ ከዓለም ዐቀፍ የግልግል ዳኝነት አንጻር የተጣለበትን ግዙፍ ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ባለሞያዎችን በእንደዚህ አይነት ተግባር ተኮር በሆኑ ሥልጠናዎች ማብቃት ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በቀጣይ ተመሳሳይ ሥልጠናዎችን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር በማዘጋጀት የባለሞያዎችን አቅም የመገንባት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናውን በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሐ ብሄር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የስራ ኃላፊዎች አቶ ሄኖክ ተስፋዬ እና አቶ ንጉሴ ትዕዛዙ ሰጥተውታል፡፡