የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋሙን ባለሙያዎች አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የተለያዩ የሥልጠናና አቅም ማጎልበቻ ሥርዓት ቀርጾ እየተገበረ ይገኛል፡፡ ከዚህ ዉስጥ በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በየወሩ የሚዘጋጀዉ የፓናል ዉይይት አንዱ ሲሆን በሀገራችን እዉቅ የሚባሉ ምሁራንን በመጋበዝና አስቀድሞ በተመረጠ ርዕስ የመነሻ ሰነድ እየቀረበ ገንቢ ዉይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡
በዚሕ ወርም “ፍትሕን ማገልገል /Serving Justice/’’ በሚል ርዕስ በወንጀል ፍትሕ ስርዓት ውስጥ የዐቃቤ ሕግ ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል በሚል ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ለ8ኛ ጊዜ በተካሄደው የፍትሕ ሚኒስቴር ወርሀዊ የፓናል ውይይት ላይ ተገኝተው የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የቀድሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ጠበቃና የሕግ አማካሪ መንበረፀሀይ ታደሰ (ዶ/ር) ሲሆኑ ፍትሕን በማገልገል ውስጥ ዐቃቤ ሕግ የማይተካ ትልቅ ድርሻ እንዳለው በተለይም በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የዐቃቤ ሕግ ድርሻ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ በሚኖረው ሂደት እና እሱን ተከትሎ በሚገኘው ውጤት ላይ ዐቃቤ ሕግ ያለውን ሚና አስረድተዋል፡፡ አክለውም ዐቃቤ ሕግ የሚከተላቸው መርሆች በሚል በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ዉስጥ ሚዛናዊ፣ ገለልተኛ፣ በቀላሉ ተደራሽ የመሆን መርሆችን በመከተል ከሕገ መንግሥቱ እና ማኅበራዊ እሴቶች አንፃር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ፍርድ ቤቶች የሚኖራቸውን ሚና በማንሳት ሰፊ ገለፃ አቅርበዋል፡፡
የሕግ የበላይነት ሲባል ተከሳሽን ማስቀጣት ብቻ አለመሆኑን ያመላከቱት ጠበቃና የሕግ አማካሪ መንበረፀሀይ ታደሰ (ዶ/ር) ይልቁንም የሕግ የበላይነት እውነት እንዲወጣ ማድረግ በመሆኑ በዚህ አንፃር ዐቃቤ ሕግ ተጠያቂነትን፣ ፍትሕን እንዲሁም ገለልተኝነትን አስጠብቆ የሕግ የበላይነት እንዲረጋግጥ የማድረግ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የተነሳው ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ ካለ ቀጣዩ ደረጃ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ በመሆኑ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ የሚያስገድደው አካል ወይም የአሠራር ሥርዓት ባይኖር እንኳን ለራሱ ህሊና እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ሲል የያዘውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት አቅርቦ አጥፊው እንዲጠየቅ ማድረግ ሙያዊ ግዴታ እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት የሚጠበቅበት በመሆኑ ከማንኛውም አካል ጋር ወገንተኛ ሳይሆን ከማስረጃ ምዘና፣ እንዲሁም ክስ ሲያቀርብ የምስክሮችንም ዝርዝር አብሮ በማቅረብ የዳኝነት አካላቱ የከሳሽና የተከሳሽን ሁኔታ እኩል እንዲመለከቱ የማድረግ እንዲሁም ፍትሐዊ፣ ግልጽ፣ እና ሕጋዊ የሆነ የክስ አቀራረብ ሥርዓትን ብቻ መከተል እንደሚኖርበት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በመድረኩ ላይ ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪን ከመያዝ ጀምሮ ፖሊስ የሚሰራቸውን የምርመራ ተግባራት የመከታተል ኃላፊነቱን፣ ገለልተኛ በመሆን የተከሳሽን ንጽህናነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንኳን ቢሆን ለፍርድ ቤት በማቅረብ ሙያዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት ጠቅሰው በአጠቃላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ተዓማኒነት ያተረፈ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ የሙያ መርሆቹን ጠብቆ መሥራት ስለሚገባው ጉዳዮች በስፋት በማንሳት ገለፃ አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም ፍትሕን ከማገልገል አንጻር በወንጀል ሕግ የዐቃቤ ሕግ ድርሻ በሚል ርዕስ በቀረበው ገለፃ መነሻነት አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮች በመድረኩ ተሳታፊዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸው በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የጋራ የሆነ ግንዛቤ ተፈጥሮ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡