ክቡር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ተኛ የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ስነ ሥርዓት ላይ ፍትሕን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፣ በሀገራችን የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንና በተለያየ ጊዜያት ያጋጠሙ የፍትሕ መዛባቶችና የመብት ጥሰቶችን በአግባቡ ለመቋጨት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች መጀመራቸውን ጠቁመው ለዚህም ማሳያ የሆነውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መፅደቅ ብሎም ፖሊሲዉን ለመተግበር የሚያስችል የፍኖተ ካርታ ዝግጅት መጠናቀቅን አውስተዋል፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንቱ አክለውም ባሁኑ ወቅትም ፖሊሲዉን ለማስተግበር የሚያስችሉ የሕግ ማእቀፎች የማዘጋግጅት እንዲሁም አስፈፃሚ ተቋማትን የማደራጀት ስራም በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
የአገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ለማስቀጠልና ብልፅግናን እዉን ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያችን ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም ነዉ፤ ለዚህ ደግሞ አገራዊ ሰላምን ማስፈንና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የቅድሚያም ቅድሚያ የሚሰጣቸዉ ቁልፍ ስራዎች ይሆናሉ፡፡
ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት የመንግሥትና የመንግሥት ፀጥታ ተቋማት ብቻና ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡: ይህ ዓመትም ህገመንግስታዊ ሥርዓትን በመጠበቅ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ሀላፊነቶችን አፈፃፀም የሚሻሻልበት ይሆናል ሲሉ ክቡር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ተናግረዋል፡፡