ወደ ኢፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የተዛወሩት የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ችሎት፣ የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና የምርት ገበያ አስተዳደራዊ ችሎት ስራ መጀመራቸውን በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት የሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው አማካሪ የሆኑት አቶ አምደሚካኤል ጌታቸው ገለጹ፡፡ የአስተዳደር ዳኝነት ችሎቶቹ ዋና ዓላማ የንግዱን ህብረተሰብ ከጸረ-ውድድር እና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት ለመጠበቅ እንዲሁም ሸማቾቹን የሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎችን ለመከላከል፣ ለነጻ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ስርዓትን ለማስፈን ብሎም የሸማቾችን ጤንነት እና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የንግድ ዕቃ አገልግሎት መስፋፋትን ለመግታት እንዲቻል እና ሸማቾች ላወጡት ዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ ዕቃ እና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እና እነዚህን ዓላማዎችን ለማስፈጸም የተቋቋሙ ናቸው ብለዋል፡፡
በንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 32 እና 33 መሠረት የቀድሞው ንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የአስተዳደር ዳኝነት ችሎት እና የይግባኝ ሰሚው አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ተቋቁመው ዝርዝር ሥልጣን እና ተግባራቸው መቀመጡንም አማካሪው አስታውሰዋል፡፡
በዚህ መሠረትም የአስተዳደራዊ ዳኝነት ችሎቱ ሥልጣን እና ተግባር በአዋጁ አንቀጽ 32 ላይ እንደተደነገገው ጸረ- ንግድ ውድድር ተግባራት በፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እና አስተዳደራዊ የገንዘብ ቅጣት መጣል ሲሆን ማለትም በአዋጁ አንቀጽ 42 መሠረት በበላይነት የተያዘ ገበያን አለአግባብ መጠቀም፣ ጸረ ንግድ ውድድር ስምምነቶች እና ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ለማስቀረት ፣ነጋዴው ከውህደት ጋር የተያያዙ ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ ሲገኝ ከዓመታዊ የሽያጭ ገቢ ላይ ከ 5 እስከ 10 በመቶ የገንዘብ ቅጣት መጣል፣ በጸረ- ንግድ ውድድር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሸማቾች እና ነጋዴዎች እንዲሁም በተደረገ ግብይት አማካኝነት ጉዳት ለደረሰባቸው ሸማቾች አግባብ ባለው ሕግ መሠረት እንዲካሱ የማድረግ፣ ተገቢ አይደለም የተባለ ድርጊት እንዲቆም የማድረግ፣ የተጎጂውን ነጋዴ የመወዳደር አቅም ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ የሚያስችል ተገቢ እርምጃ መውሰድ እና የአጥፊውን የንግድ ፈቃድ እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል ሲሉ አቶ አምደሚካኤል ተናግረዋል፡፡
ይግባኝ ሰሚው አስተዳደራዊ ችሎት ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 33 መሠረት በአስተዳደራዊ ችሎቱ በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰጡ ውሳኔዎችን በይግባኝ የማየት ፣ባለስልጣኑ በውህደት ጉዳይ እና በአሳሳች ማስታወቂያዎች ላይ የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች በይግባኝ አይቶ የማረም ሥልጣን እንዲሁም ሌሎች በርካታ ተግባራት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የቀድሞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ችሎት የተቋቋመው በአዋጅ ቁጥር 551/1999 (እንደተሸሻለ) መሠረት ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 6 (10) እና 7 መሠረት የተሰጠው ሥልጣን በምርት ገበያና እና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚፈጸሙ የግብይት ሕግጋት ጥሰተቶችን መርምሮ አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድ እና ባለስልጣኑ ባወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2000 (እንደተሸሻለ) ክፍል አስርና አስራ አንድ ለችሎቱ የተሰጠው የመዳኘት ሥልጣን ነው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በአስተዳደራዊ የዳኝነት ችሎቱ ግብይት ፈፃሚዎች (የምርት ገበያ አባላት ነጋዴዎች)የክፍያና ርክክብ ተቋማት ወይም ባንኮች ኃላፊዎቻቸው፣ ሰራተኞቻቸውና ወኪሎቻቸው፣ገለልተኛ ኦዲተሮች፣ የምርት ገበያው ኃላፊዎችና ሰራተኞች፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ማንኛውም ጥቅም ያለው ሌላ ሰው በችሎቱ በከሳሽነት ወይም በተከሳሽነት ሊቀርቡ እንደሚችሉም አማካሪው ገልጸዋል ፡፡
አስተዳደራዊ ችሎቱ በዋናነት የምርት ግብይት ሕግጋትን የሚጠቀም ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የቀድሞው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር551/1999 (እንደተሻሻለ)፣ እና የገበያው የውስጥ ደንብ፣ገበያው የሚሰራባቸው ማንዋሎች፣የባለስልጣኑን እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚያወጣቸው የምርት ግብይት ነክ መመሪያዎች፣ ትእዛዞች፣ እንዲሁም አግባብነት ያላቸው ንግድና ንብረት ነክ የሀገሪቱ ህጐችንና የምርት ግብይት ሕግጋትን እንደሚጠቀም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም አስተዳደራዊ ችሎቱ የሚቀርቡለትን ጉዳዮች በመመርመር በአንድ መዝገብ እስከ 750 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የመጣል፣ የእውቅናና ስራ ማስጀመሪያ ፈቃድ የማገድ፣ የእውቅናና ስራ ማስጀመሪያ ፈቃድ የመሰረዝ፣ ጥሰት እንዲቆም የማዘዝ፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሚከስበት ጉዳይ እንደ ሁኔታው የሚኒስቴሩ ውሳኔ እንዲጸና፣ እንዲሻር፣ እንዲሻሻል ወይም ተመልሶ እንዲታይ የመወሰን፣ የወንጀል ጉዳይ ሲያጋጥም ደግሞ ለሚመለከተው የፍትሕ አካል የማስተላለፍ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ሲሉ በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት የሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው አማካሪ የሆኑት አቶ አምደሚካኤል አብራርተዋል፡፡