የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ተቋማት በሀገራችን ኢትዮጵያ በሚቋቋሙበትና ፈቃድ የሚሰጥበትን አሠራር አስመልክቶ ባዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ዙሪያ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት አካሂዷል፡፡
ረቂቅ ህጉ የተዘጋጀው በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 18 ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ(የአሁኑ ፍትሕ ሚኒስቴር) የግልግል ዳኝነት ማዕከላትን አስመልክቶ ፈቃድ እንዲሰጥ፣ እንዲያድስ፣ የሚቋቋሙበትን መስፈርቶች እንዲያወጣና እንዲቆጣጠር የተሰጠውን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ ሲሆን ረቂቅ ህጉ በአንድ መልኩ የሀገራችን ባለሙያዎች ፈቃድ ወስደው ዓለም ዓቀፍ አገልግሎት እንዲሰጡ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን በሌላ መልኩ ዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት አገልግሎት በተደራጀና ዘመናዊ በሆነ መልኩ በመስጠት የሚጠቀሱት የግልግል ዳኝነት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሀገራችን የሚመዘገቡበትና ፈቃድ ወስደው የሚንቀሳቀሱበት ያካተተ መሆኑን በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሃብሄር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ንጉሴ ትዕዛዙ ተናግረዋል፡፡
ረቂቁ ወደፊት የሚሰጠው የግልግል ዳኝነት አገልግሎት በተደራጀና በተጠናከረ እንዲሁም ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ ፈቃድ በሚሰጣቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዓለም ዓቀፍ ማዕከላት እንዲሰጥ በማድረግ አገልግሎቱ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን በቀጠናው ላይ የንግድ ነክ አለመግባባቶችን በመፍታት አገራችን እንደ ተመራጭ የግልግል ዳኝነት አገልገሎት መዳረሻ እንድትሆን በሚያግዝ ደረጃ ታልሞ መዘጋጀቱን ተጠቅሷል፡፡ ይህን ለማድረግም በተግባር የሚታዩትን አስቻይ ሁኔታዎችና ክፍተቶች በመፈተሽ የሌሎች ሀገራትንም ልምድ ያካተተ ጥናት በማከናወን ከጥናቱ የተገኘውን ምክረሃሳብ መሠረት በማድረግ የሕግ ረቂቁ እንደተዘጋጀ ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራሉ ገልፀዋል፡፡
በአጠቃላይ ህጉ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ የግልግል ዳኝነት ማዕከላት በሚሰጡት አገልግሎት የንግድ ስርዓቱ ቀልጣፋና ራሱ በሚመርጠው ሙያተኛ እንዲዳኝ እድል እንደሚፍጠር፣ የፍርድ ቤት ጫናን በማቅለል ለፍትሕ ስርዓቱ መሻሻልን እንደሚያግዙ፣ በቀጠናው ላይ ያለውን ንግድ ነክ አለመግባባት ለማየት ሀገራችን ተመራጭ መቀመጫ እንድትሆን በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚያስችል እና ሌሎች ተጨማሪ ፋይዳዎች እንደሚኖሩት የተገለፀ ሲሆን በጥቅሉ የፍትሕ ስርዓቱ አጋዥ በመሆን በዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃትና ትጋትንም እንደሚጨምር ተጠቁሟል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ በዘርፉ እየሰሩ የሚገኙ ተቋማት፣ በግል ዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎች፣ በቀጣይ በህጉ ትግበራ ላይ ቀጥተኛ ሚና ያላቸው የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የሕግ ቢሮዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሳታፊ እንደነበሩ የተገለፀ ሲሆን ከተሳታፊዎችም ለረቂቅ ህጉ ግብአት የሚሆኑ ሀሳብና አስተያየቶች መገኘቱም ተጠቅሷል፡፡
በቀጣይም ረቂቁን የበለጠ ለማዳበር የሚያስችሉ መሰል መድረኮች እንደሚመቻቹና የተገኙ ምክረ ሀሳቦችን አካቶ ረቂቅ ህጉን በማጠናቀቅ ለሚመለከተው አካል የመላክ ስራ እንደሚከናወን ተገልጧል፡፡