አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቶችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ምክክር ተደረገ

Consultation Held to Enhance the Effectiveness of Administrative Tribunals

የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቀላቀሉት የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ ችሎት፣ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና የምርት ገበያ አስተዳደራዊ ችሎት ስራ ከጀመሩ 2 ዓመት ቢያስቆጥሩም በሚፈለገው ደረጃ ቀልጣፋና ውጤታማ ስራዎችን እያከናወኑ ባለመሆኑ በችግሮቹና በቀጣይ የስራ ተልዕኮዎች ላይ ያለመ ምክክር ተደርጓል፡፡

ምክክሩን የመሩት የመንግሥት የሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ አስተዳደራዊ ችሎቶቹ ስራቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዳያከናውኑ እንቅፋት የሆኑ የአደረጃጀት፣ የአሠራርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳቦችን በመቀበል ስራውን የተሻለ አደረጃጀትና የስራ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ መፍትሄዎችን አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር ያለውን የስራ መስተጋብር በማጠናከርና ቀጣይነት ያለው ምክክር በማድረግ፣ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ያለውን የተሻለ ልምድ እና ተሞክሮ አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመጠቀምና አስተዳደራዊ ችግሮችን በአፋጣኝ በመፍታት ችሎቶቹ የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አጽዕኖት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡

ችሎቶቹ በዋናነት በሸማቹ ማኅበረሰብ፣ በነጋዴው ማኅበረሰብ እና በተቆጣጣሪ የመንግሥት ተቋማት የሚቀርቡ ከንግድ ውድድር፣ ሸማቾች ጥበቃ እና ከምርት ገበያ የግብይት ስርዓት ጋር በተገናኘ የሚቀርቡ ክሶችን በመቀበል ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ ከክቡር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታው በተጨማሪ የፌዴራል ግብር ይግባኝ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ አያሌው እና የፍትሕ ሚኒስቴር አመራሮች በመገኘት ማብራሪያና ምክረ ሀሳቦችን አጋርተዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የሶስቱ ችሎቶች ለአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና ሲባል የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ ወደሚገኝበት ጨለቀቅ ሕንጻ የተዘዋወረ መሆኑን በመግለጽ የችሎቶቹን አገልግሎት ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሜክሲኮ ጨለለለቅ ሕንጻ ላይ በሚገኘው ቢሯቸው መስተናገድ የሚችል መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

Tagged Under: administrative Administrative Procedure commercial Commercial Law competition competition law consumer Consumer Protection Dispute Resolution effectiveness Efficiency government regulation judicial judicial efficiency law legal legal framework Legal Reform organizational structure Policy Implementation protection reform Regulation Stakeholder Consultation Trade trade regulation
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች