የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 23 / 2018 ዓ.ም ባካሔደው ሰባተኛ መደበኛ ስብሰባው የምክር ቤት አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች የፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርያስላሴ በምክር ቤቱ ተገኝተው ምላሽና ማብራርያ ሰጥተዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ የምክር ቤት አባላት የሕግ የበላይነትንና የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መጠበቅን በተመለከተ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ የዜጎች መብቶች እንዲከበሩ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት እንዲሁም በሕዝብ ሥም የሚፈጸሙ የተለያዩ ወንጀሎችን ከመከላከል እና ጥፋተኞችን በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር በአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ሚኒስትሯ ሲመልሱ በሚኒስቴሩ የሕግ የበላይነትን እንዲጠበቅ በማድረግ የዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ እንዲከበሩ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል ።
ክብርት ሚኒስትሯ እንደገለፁት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በየደረጃው አስፈላጊው የሪፎርም ሥራዎች መተግበራቸውን አንስተው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊ የሆኑ የለውጥ ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዜጎችን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን በተመለከተ ማንኛውም አካል የመብት ጥያቄ ሲኖረው ሕገ መንግሥቱን እና የሀገሪቷን ሕጎች ባከበረ መንገድ ሊቀርብ ይገባል ያሉ ሲሆን ሚንስትሯ፤ ከሕግ ውጭ የሆኑ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን በየደረጃው ተጠያቂነት እንደሚኖርም ነው ያብራሩት።
ከፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥና ከወንጀል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ለተነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎች የወንጀል ጉዳዮች በባህሪያቸው ውስብሰብነት ያላቸው እና ዝርዝር መረጃና ማጣራትን የሚፈልጉ በመሆናቸው ጊዜ ሊወስዱ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም የወንጀል እና የፍትሕ ጉዳዮች ዝርዝር መረጃ ማጣራትን እንደሚጠይቅና የማጣራቱ ሥራ ጊዜ ተወስዶ በጥንቃቄ የሚሰራ መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው በየደረጃው ምላሽ እንደሚሰጥም ክብርት ወ/ሮ ሐና አርያስላሴ አስረዳታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡