በግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች ውሎች አተገባበር ሂደት ለክርክር የሚያጋልጡ ስጋቶች የሚገመገሙበትና የሚቀረፉበትን አሰራር ለመዘርጋት በተጠና ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ

Large Government Projects Administration Challenges Discussed

በግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ውሎች አተገባበር ሂደት ለክርክር የሚያጋልጡ ስጋቶች የሚገመገሙበትና የሚቀረፉበትን አሠራር ለመዘርጋት በተጠና ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ።

የግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ውሎችን አፈጻጸም በተሻለ ለማሳደግ እና ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለታለመላቸው የሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ለማስቻል የሚረዳ የአሠራር ስርዓት ለመቅረጽ እንዲያስችል ታስቦ ሲከናወን የነበረ የዳሰሳ ጥናት ተጠናቅቆ ፕሮጀክቶችን በማስፈጸም ረገድ ኃላፊነት ካለባቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱ ወቅት የግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ውሎች አፈጻጸም ከፍተኛ ክፍተት የሚስተዋልበት፣ ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ እና የሀገርን ውስን ሀብት እያባከነ የሚገኝ ወጥ ስርዓት ያልተበጀለት እንደሆነ ተመልክቷል። ከፕሮጀክት ቅድመ ጥናት ጀምሮ፣ ተዋዋዩን ከመምረጥ፣ የውል ድርድር ከማድረግ፣ ረቂቅ ውል ከማዘጋጀት እና የውሉን አፈጻጸም በአግባቡ ከመከታተል ጋር ተገናኝቶ የሚስተዋሉ ሰፊ ክፍተቶች ለከፍተኛ የጥራት መጓደል እና ለፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ብሎም ለተራዘመ ክርክር ምክንያት እየሆኑ እንደሚገኙ የጥናቱ ግኝት አሳይቷል። በክፍትተ ደረጃ ከተለዩት መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በፕሮጀክት አስፈጻሚ አካላት መካከል ተገቢው ቅንጅታዊ አሠራር አለመኖሩ እንደሆን በተሳታፊዎች ተገልጿል።

ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በተደረገው ውይይት ጥናቱን ለማዳበር የሚያስችል ብዙ ግብዓት የተገኘ ሲሆን ለክርክር ሊያጋልጡ የሚችሉ ስጋቶችን አስቀድሞ ለመለየት፣ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ እና የውል አፈጻጸሙን በአግባቡ በመከታተል ረገድ አስፈጻሚ በሆኑ ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባውን ቅንጅት ለመዘርጋት የሚያስችል የአሠራር ስርዓት ለመቅረጽ ያግዛል። የሚዘጋጀው የአሠራር ስርዓት በተለይ የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ሥርዓትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1210/2012 ላይ የፕሮጀክት አስፈጻሚ ተብለው በተለዩ ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባውን ቅንጅት ታሳቢ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በማኑዋል ደረጃ የሚዘጋጀው የአሠራር ስርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከመከሩበት በኋላ ወደስራ ይገባል ያሉት በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሃብሄር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት አቶ ሄኖክ ተስፋዬ ናቸው።ጥናቱ ከ USAID/Feteh Activity በኢትዮጵያ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በዘርፉ ልምድ ባላቸው የሕግ ባለሞያ አቶ ፊሊጶስ አይናለም ተከናውኗል።

Tagged Under: administration • Administrative Procedure • contract • contract administration • Corruption • due diligence • engagement • federal • Federal Government • framework • Government • Government projects • Implementation • legal • legal framework • policy recommendations • procurement • project • project implementation • Project Management • projects • public • public procurement • regulatory • Regulatory Framework • stakeholder • Stakeholder Engagement • USAID
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች