የአስተዳደር ተቋማት የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1183/2012ን አክብሮ መመሪያ ከማውጣት እና አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመስጠት አንጻር እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ለተጠሪ ተቋሞቻቸው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሥልጠና በመስጠት የሚተገበር ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጁ አተገባበር ላይ ክትትል ባደረገባቸው ተቋማት ለአዋጁ አለመተግበር በዋናነት ተጠቃሽ ከሆኑት ምክኒያቶች አንዱ ስለ አዋጁ ያለ የግንዛቤ እጥረት መሆኑ ሥልጠናውን ለመስጠት ምክንያት መሆኑ በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ለአዋጁ መተግበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ለተቋማት የሥልጠና መርሀ-ግብር አውጥቶ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ተጠሪ ተቋማት በአዋጁ አስፈላጊነት፣ ዓላማ እና ይዘት ዙሪያ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሁለተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ንቅናቄ ነሀሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ለፕላን እና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ለሆኑት የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በአዋጁ አስፈላጊነት፣ ዓላማ፣ ጠቀሜታ እና ይዘት ዙሪያ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
ሥልጠናውን የሰጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ሕጎች ተፈጻሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ትብለጥ ቡሽራ ሲሆኑ በአዋጁ ዙርያ የሚስተዋሉ ግንዛቤ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችል ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኃላ አዋጁ ለወጣለት ዓላማ በተገቢው ሁኔታ ተግባር ላይ ቢውል ሕገ-መንግስቱን እና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ከማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመቅረፍ እና ተቋማትን ከመገንባት አንጻር ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታም ያጎለብታል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም መድረኩ ለፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆኑት ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ ባስተላለፉት መልዕክት ተጠናቋል።
ቀደም ብሎ በተያዘ መርሀ ግብር በተመሳሳይ 121 ለሚሆኑ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት መካከለኛ አመራሮች በአዋጁ ዙሪያ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን ለሌሎች ተቋማት አመራሮች ተመሳሳይ ሥልጠናዎች መሰጠቱ ይቀጥላል፡፡