የንግድ እና ሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ኮሚቴ አባላት እና የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሰብዓዊ መብት ተጠሪዎች በቀጣይ በሚካሄዱት አገር ዓቀፍ የንግድ እና ሰብዓዊ መብቶች ድርጊት መርሓ ግብር የምክክር መድረኮች ዙሪያ ምክክር አደረጉ፡፡
በምክክር መድረኩ የንግድ እና ሰብዓዊ መብቶች የመመሪያ መርሆዎችን፣ በንግድ እና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሓ ግብር ሂደት የአገር ዓቀፍ ምክክር አስፈላጊነት እና የመተግበሪያ ዘዴዎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከመላው ዓለም በጉዳዩ ላይ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው አገራትን ልምዶች የሚመለከቱ ገለጻዎች ቀርበዋል፡፡
በዚህ ሰኔ 26 ቀን 2017 በተጀመረው የምክክር መድረክ ሁለተኛ ቀን ውሎም በንግድ እና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሓ ግብር ላይ ውጤታማ እና ትርጉም ያለው ውይይት ለማካሄድ ያግዝ ዘንድ የተዘጋጀው የምክክር ማስፈጸሚያ ረቂቅ ሰነድ ቀርቦ ከተሳታፊዎች አስተያየት ተሰብስቧል፡፡
ከአገር ዓቀፍ ምክክር መድረኮቹ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት በተጨማሪ በተከናወነው ብሔራዊ ጥናታዊ ዳሰሳ ግኝት መሠረት የድርጊት መርሓ ግብር ቀረጻው በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደሚጀመር በፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አወል ሱልጣን በመድረኩ ጅማሮ ላይ አንስተዋል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ምክትል ሬዚደንት ተወካይ ቻሩ ቢስት ኢትዮጵያ የንግድ እና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሓ ግብር ነድፍ ተፈጻሚነቱን ለመከታተል እያሳየች ያለችውን ጥረት አድንቀው በሂደቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑን አረገግጠዋል፡፡
መድረኩን የፍትሕ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከዳኒሽ የሰብዓዊ መብት ተቋም እና ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡