የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 (6) መሠረት የፌዴራል መንግስቱ ሕጐች ተግባራዊ መደረጋቸውን እና አተገባበራቸውም ወጥነት ያለው መሆኑን የማረጋገጥ፤ እንዲሁም አስፈፃሚ የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች ሥራዎቻቸውን በሕግ መሠረት ማከናወናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ህጎች ለወጡበት ዓላማ ወጥነት ባለዉ መልኩ መፈፀማቸዉን የማረጋገጥ ስራ ከሚሰራባቸው መንገዶች አንዱ ከግለሰቦች የሚቀርቡ አቤቱታዎች መነሻ በማድረግ ነዉ፡፡
በዚሁ መነሻነት በወርሃ ጥር 2015 ዓ.ም መጨረሻዎች አካባቢ ብዛታቸዉ ከ30 የሚበልጡ የጡረታ መብት ተጠቃሚዎች በተወካዮቻቸዉ አማካኝነት በመንግሥት መ/ቤቶች የአገለግልንበት የአገልግሎት ዘመን በግል ድርጅት ሰራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በኩል አልተያዘልንም፡፡ ይህ የሆነዉ ደግሞ የመንግሥት ሰራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የተደራጀ የዋስትና መለያ ቁጥር እና ማህደር በእኛ በኩል የለም በማለት ከዋስትና መብት ጋር ተያያዥነት ያላቸዉን ማስረጃዎች ባለማስተላለፉ ነዉ በማለት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ከላይ እንደተገለፀዉ ፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት እና ለቀረበዉ አቤቱታ መፍትሄ ለመስጠት ያስችል ዘንድ አቤቱታ አቅራቢዎችን፤ የመንግሥት ሰራተኞች እና የግል ድርጅት ሰራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የስራ ክፍል ሃላፊዎችን ጠርተን በማወያየት ከዉይይቱ የተገኘዉን ሀሳብ መነሻ በማድረግ ከጡረታ መብት ጋር ተያያዥነት ያላቸዉን አዋጅ ቁጥር 1267/2014 እና 1268/2014 ዓ/ም ጋር በማገናዘብ ከማስረጃ ትልልፍ ጋር በተያያዘ ያለዉ የሕግ አረዳድ ክፍት ላይ 1ኛ.መለያ ቁጥር ኖሯቸዉ መረጃዎች ያልተዳራጀላቸዉን የጡረታ ባለመብቶች በተመለከተ ሁለቱም ተቋማት አንዱ ለሌላዉ ማህደሩን አደራጅቶ እንዲልክ 2ኛ. የዋስትና መለያ ቁጥር እና ማህደር የሌላቸዉን የጡረታ ባለመብቶች በተመለከተ ደግሞ ሁለቱም የማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደሮች በጡረታ ባለመብቶቹ አማካኝነት የሚቀርቡ መረጃዎችንና ከሰሩባቸዉ ተቋማት ተጨማሪ ማስረጃዎችን በራሳቸዉ መንገድ በማሰባሰብ አደራጅተዉ በማስተናገድ ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈቱ የሚሉ ምክረ ሀሳቦችን በማስቀመጥ ሁለቱም የዋስትና አስተዳደሮች በተሰጠዉ ምክረ ሀሳብ መሠረት እንዲያስፈፅም ተጠሪ ለሆኑለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማሳወቅነዉ መሠረት ባንኩ ለሁለቱም የዋስትና አስተዳደር መስሪያ ቤቶች ምክረ ሀሳቦችን ልኮ መ/ቤቶቹ የተሰጠዉን ምክረ ሀሳብ ተቀብለዉ ተግባራዊ በማድረግ ለችግሩ መፍተሄ እየሰጡ መሆኑን ከአቤቱታ አቅራቢዎች እና በእኛ በኩልም ባደረግነዉ ማጣራት ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
በዚህም መሠረት ከማኅበራዊ ዋስትና ጋር በተያያዘ ለዜጎች መብት ጥሰት እና ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ የሆነዉ የማስረጃ ትልልፍ ጉዳይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አጋዥነት እና በመንግሥት እና በግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደሮች ለሕግ ተፈፃሚነት ባላቸዉ ቀና ትብብር አማካኝት በዘላቂነት የተፈታ ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤታችን ችግሩ በዘላቂነትና በአፋጣኝ እንዲፈታ ቀና ትብብር ላደረጉት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲሁም ለሁለቱም ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደሮች የላቀ ምስጋና ያቀርባል፡፡
የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር