ለህግ ማርቀቅ ስራ የሚውሉ ቃላትና ሐረጋት ወጥ የሆነ ስርዐተ -ፅህፈት እንዲኖራቸዉ ስርአትን ለመዘርጋት የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

Financial Support Agreement Signed to Establish a Standardized Writing System for Legal Drafting Terminology

ህጎች በሚረቀቁበት ጊዜ ሕግ ነክ ቃላቶች ወጥ የሆነ ስርአተ-ፅህፈትን በተከተለ መንገድ እንዲሆን የሚያስችል ሥርዓትን ለመዘርጋት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር፣የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ተቋም እንዲሁም ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፎሎዉ ሽፕ በዛሬዉ እለት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በዛሬዉ እለት በሶስቱ ተቋማት የተደረገዉ ስምምነት በዋናነት ይህንኑ ስራ ለማስጀመር የሚያስፈልገዉን የገንዘብ ድጋፍ የተመለከተ ሲሆን ድጋፉን ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፎሎዉ ሺፕ የሚሸፍን ይሆናል፡፡

ከዚህ ቀደም የአማርኛ የሕግ መዝገበ ቃላት ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ሲሆን ይኸኛዉ ፕሮጀክትም ህጎች ሲረቀቁም ሆነ መሰል ህጎች ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ሲተረጎሙ ወጥ የሆነ የፊደል አጠቃቀም ሥርዓትን እንዲጠቀሙ በማድረግ ሁሉም ህጎች ተመሳሳይ የሆነ የቃላት ትርጉምና የፊደል አጠቃቀም ሥርዓትን በመዘርጋት ወጥ የሆነ ስርአተ-ፅህፈት እንዲኖራቸዉ የሚያስችል መሆኑ በስምምነቱ ተገልፆል፡፡

ስርአቱ ተግባራዊ ሲደረግ ህጎች በሚረቀቀቁበት ወቅት የቃላትን አዉዳዊ ፍቺ ለማግኘት የሚስተዋሉ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት የሚያስችል ሲሆን በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ዉጤቶችን በመጠቀም ፓርታሎችን በማዘጋጀት በቀላሉ በመፈለግ አዉዳዊ ፍቻቸዉን ማግኘት የሚያስችል አሠራር የሚካተትበት ይሆናል፡፡

የሕግ ስርአቱን በማዘመን ሂደት ዉስጥ የሕግ ማርቀቅ ስራ አንደኛዉ መሆኑንና ጠንካራ የሕግ ሥርዓት መሰረቱ ከአወጣጡ እንደሚጀምር የተናገሩት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ከዚሁ ጋር በተገናኘ ባለፉት አመታት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንና ከነዚህ ተግባራት ዉስጥም የሕግ አረቃቀቅ ማንዋል አንደኛዉ መሆኑን አንስተዉ በተጨማሪም የቃላት ትክክለኛ የአማርኛ ትርጉምና የአፃፃፍ ሥርዓት መሠረታዊ ከመሆኑ ባሻገር የሕግ ጥራትን በማስጠበቅ ረገድም አንደኛዉ መሆኑንተናግረዋል።

አያይዘዉም ሕግ የሚያረቁ ባለሙያዎች ህጎችን በሚያዘጋጁበት ወቅት የቋንቋ አጠቃቀማቸዉን የሚመለከት ሥርዓት ከዚህ ቀደም አለመኖሩን አንስተዉ ይህ ስርአተ- ፅህፈት ሁሉም ባለሙያዎች በተቻለ መጠን ወጥነት ያለዉ ትርጉም ያላቸዉን ቃላት እንዲጠቀሙና ቃላቶቹ አቻ የሆነ ትርጉማቸዉ በቴክኖሎጅ ተደግፎ የሚገኝበት መንገድ የሚዘረጋ በመሆኑ ፋይዳዉ የጎላ መሆኑን አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ኢንሲቲቲዩት ዳይሬክተር ዶክተር ዮሐንስ አድገህ በበኩላቸዉ ስምምነቱ በሕግና ፍትሕ ዘርፍ የሚረቀቁ ህጎች፣ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ሌሎች ሰነዶች ወጥነት ባለዉ መንገድ የተሻለ የፅህፈት ሥርዓት የተከተሉ እንዲሆኑ ለማስቻልና የሕግ ምሁራንና ተማሪዎች ሕግ በሚያረቁበት ወቅት አጋዥ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘመኑን የዋጁ አካሄዶችን በመከተል ስርአተ-ፅህፈትን በማሻሻል ተግባቦቱን የተሳለጠና ግንኙነቱ ያማረ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል እንደሚሆን ገልጸዉ በቀጣይም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር አብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፎሎዉ ሺፕ ፕሬዝዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ በበኩላቸዉ ባለፉት በርካታ አመታት በሕግ የበላይነት ዙሪያ ድርጅታቸዉ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታዉሰዉ ወጥ የሆነ የቋንቋ ትርጓሜ ያለዉ ተቋም መፍጠር ለስራዎች መሳካትና ወጥነት ያለዉ ስራ እንዲሰራ ያለዉ ሚና የጎላ መሆኑን አንስተዉ ድርጅታቸዉ ይህንን ስራ በእዉቀትና በገንዘብ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ስምምነቱን በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የፍትሕ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላየሁን ይርጋ፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል ዮሐንስ አድገህ (ዶ/ር) በጀስቲን ፎርኦል ፕሪዝን ፎሎዉ ሺፕ በኩል ደግሞ ፓስተር ዳንኤን ገብረስላሴ አማካኘነት ተፈርሟል፡፡

Tagged Under: act • agreement • Budget • court • dar • decree • draft • drafting • Economic • finance • financial • financial support • financial system safety and soundness • fiscal • judge • judicial • judiciary • law • legal • Legal drafting • legislation • lis • Policy • port • proclamation • Regulation • standard • statute • support • system
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች