የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በማኅረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ውስጥ ለሚያገለግሉ የሲዳማ ክልል ሽማግሌዎች (ጭሜዬዎች) ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የቆየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በሀዋሳ ከተማ ተሰቷል።
የሥልጠና መድረኩ በዋናነት አለመግባባትን በባህላዊ መንገድ በመፍታት ሂደት የሽማግሌዎች አስተዋፆ ጉልህ በመሆኑ የሰብዓዊ መብት መርሆዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ እና የለውጥ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኖህ ታከለ በሥልጠና በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሀገር ደረጃ በፍትሕ ዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የ3 ዓመት የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን አቅድ ፍኖተ ካርታ በትግበራ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በፍኖተ ካርታው ከሚተገበሩ አምዶች ውስጥ አንዱ “የመሰረተ ማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕ አገልግሎትን ማሳደግ” ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ይህን አምድ ገቢራዊ ለማድረግ የፍትሕ ሚኒስቴር በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ይህ ሥልጠናም የእቅዱ አንዱ አካል በመሆኑ ሽማግሌዎች ስለሰብዓዊ መብቶችና ህገ-መንግስቱ ያላቸውን ግንዛቤ ማጎልበት የተሻለ ማኅበረሰብ ላይ የተመሰረተ የፍትሕ አሰጣጥን የሚያመቻችና ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ከሀገር ሕግ መስፈርቶች ጋር የሚያስማማ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊ የሆኑ ሽማግሌዎች በበኩላቸው ፍትሕ ሚኒስቴር የሥልጠና መድረኩን በማመቻቸቱ አመስግነው፤ ሥልጠናው መሠረታዊ መብቶችን በማስከበር ማህበረሰቦቻቸውን በተሻለ መንገድ ለማገልገል እንደሚረዳቸውም አስታውቀዋል። አክለውም ፍትሕ ሚኒስቴር እነዚህን የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ወደ ተጨማሪ አከባቢዎች በማስፋት፣ በባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች እና በመንግሥታዊ የሕግ መስፈርቶች መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የሥልጠና መድረኩ ሂል ኢንስቲዩት እና ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ባደረጉት ድጋፍ የተካሄደ ነው።