የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከስርዓተ-ጾታ አካቶ ጋር በተያያዘ በተደረገ ጥናት ሪፖርት ዙሪያ ውይይት አካሔደ

FDRE Ministry of Justice Discusses Report on Gender Mainstreaming Study

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከስርዓተ-ጾታ አካቶ ጋር ተያይዞ በተደረገ የኦዲት ጥናት ሪፖርት ዙሪያ ከተቋሙ አመራሮች ጋር ሰኔ ዐ6 ቀን 2ዐ15 ዓ.ም. በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ውይይት አካሂዷል፡፡

በተቋሙ የሴቶችና የባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጥናቱን በተቋም ደረጃ በየ5 አመቱ ከማካሄዱ ጋር ተያይዞ በ2015 በጀት ዓመትም ከስርዓተ-ጾታ ጋር በተደረገ የኦዲት ጥናት ዙሪያ የግኝት ሪፖርቱን ለተቋሙ አመራሮች አቅርቧል፡፡

የጥናቱም ዋና ዓላማ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ በተጨባጭ የሥርዓተ-ጾታ ማካተትና የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ከማረጋገጥ አንጻር የደረሰበትን ደረጃ፣ ያለውን ጥንካሬ እንዲሁም ያልተፈቱ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው መሠረታዊ የመፍትሔ እርምጃዎችን በግልፅ ማመላከት መሆኑን በቀረበው የኦዲት ሪፖርት ላይ የተገለጸ ሲሆን በነዚህ ዙሪያ የተደረገው ጥናትም በኦዲት ግኝቱ ላይ ተካቶ ለመድረኩ ተሳታፊዎች በዝርዝር ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙ የያዘውን ራዕይና ተልእኮ ለማሳካት ይቻል ዘንድ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ የተቋሙ የውስጥ ሰራተኞች እንዲሁም የውጪ ወንድ እና ሴት ተገልጋዮች በእኩል ደረጃ ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ሌላኛው ዓላማው መሆኑንም በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል፡፡ በቀረበው ሪፖርት ላይም ከመድረኩ ተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የሪፎርም እና የተቋም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስተር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነህብርሀን እንደተናገሩት ከስርዓተ-ጾታ አካቶ አንጻር ሊተገበሩ የሚገባቸው ሶስት መሠረታዊ ነገሮችን ያነሱ ሲሆን እነሱም ዕኩል እድል ፣ምቹ ሁኔታ እና ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ አሠራር ናቸው ብለዋል፡፡ እነዚህን ሶስት ነገሮች ለማሳካት በአመራሩና በባለሙያው መካከል መሠረታዊ የሆነ ግንዛቤ መጨበጥ እንዳለበትም አክለዋል፡፡

በሪፖርቱ ላይ እንደተመላከተው የስርዓተ-ጾታ አካታችነትን ከመተግበር አንጻር የተሻሉ ውጤቶች እንዳሉ ሁሉ እንደተቋም የሚቀሩ እና ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ተግባራት መኖራቸውንም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩልም ፍትሕ ሚኒስቴር ህጎችን የማርቀቅ ኃላፊነት ያለበት ተቋም እንደመሆኑ መጠን በሕግ ማርቀቁ ሂደት ውስጥ የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት የሚያጎሉና የሚያሰፉ የሕግ ማዕቀፎች ማዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ሴቶችን ከማብቃት አንጻር ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው ሲገልጹ ተተኪ አመራሮችን ከመተካት አኳያ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በተሻለና ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ በሚሆን ደረጃ ፍትሕ ሚኒስቴር መሥራት እንዳለበት አመላክተው በዚህ ረገድ የተቋሙ ሁሉም የስራ ክፍሎች የስርዓተ-ጾታን ጉዳይ በዕቅድ ውስጥ በማካተት ከመደበኛ ስራቸው ጋር ዕኩል ትኩረት በመስጠት ሊከውኑ እንደሚገባ እንዲሁም ጉዳዮን ተቋማዊ ባህል በማድረግ የክትትልና ድጋፍ፣የግምገማ ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

Tagged Under: audit • audit report • building • capacity • Capacity Building • democratic • development • Equality • FDRE • federal • federal democratic republic of ethiopia (fdre) • gender • Gender Equality • gender inclusion • gender mainstreaming • Leadership • Leadership Development • Legal Frameworks • mainstreaming • policy recommendations • report • republic • succession planning • women's • Women's Rights
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች