የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ፋሲካው ሞላ ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው የተቋማቸውን የስራ እንቅስቃሴ ለመመልከትና የጥራት ደረጃ የክብር ተሸላሚ መሆናቸውን መሠረት በማድረግ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት መገኘታቸውን አመስግነው በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የተከወኑ የለውጥ ስራዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተክትሎ በሀገር ደረጃ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሕግ ማሻሻያ ከተደረገ ጀምሮ ባለፉት አምስት አመታት በባለሥልጣን መስሪያቤቱ በሁለት ምዕራፍ የተከናወኑ ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችን ያብራሩ ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ የዘርፍ ዳሰሳዊ ጥናት በማድረግ መልካም ጎኖችንና ተግዳሮቶችን በመለየት የመፈፀምና የማስፈጸም አቅሙ የተገነባ ባለሙያ መፍጠርን የትኩረት መስክ በማድረግ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ የትኩረት መስክም አመለካከቱና አቅሙ የተገነባ ሰራተኞችን በመፍጠር ለሀገራዊ ሪፎርሙና ለተቋሙ አስተዋፅኦ የሚደርግ የሰው ኃይል ለመገንባት ጥረት መደረጉን አክለዋል።
ሌላው በዚህ ምዕራፍ የተሰሩ ስራዎች በመንግሥት ደረጃ የተወሰደውን የሕግ ሪፎርም ማሻሻያ በማድረግ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ሊያሳድጉ የሚችሉ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባት መቻሉን አንስተዋል ክቡር ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ። የጎንዮሽና የተዋረድ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አውስተው በአሁኑ ወቅት የሁለተኛ ተቋማዊ የሪፎርም ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ እና በዚህ ምእራፍ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ተለምዶአዊ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በመቀየርና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑንና የምዝገባ፣ የግምገማ፣ የቁጥጥርና የምርመራ ስራዎችን የሚሰራ ተቋማዊ አደራጃጀት በመፍጠር ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተቋማዊ ልህቀትን መፍጠር በሚያስችል መልኩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህን የሪፎርም ስራዎች በመከወን በመንግስታዊ ተቋማትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል የተሻለ ግንኙነት መፍጠር መቻሉን እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለዴሞክራሲና ልማት አስተዋፅኦ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋማዊ ሪፎርሞቹ በመከወናቸው ከኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዓለም ዓቀፍ የመመዘኛ ስርኣትን በማለፍ ባለስጣልን መስሪያቤታቸው የከፍተኛ አድናቆት ተሸላሚ መሆኑን ያወሱት አቶ ፋሲካው የሽልማቱ ውጤት የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች የጋራ ጥረት እንዲሁም ፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ በባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር የመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ መንግሥት በሀገር ደረጃ ከወሰዳቸው አበይት የሪፎርም ስራዎች ውስጥ አንዱ ለተቋማት ግንባታ ማነቆ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል ነው። አያይዘውም መንግሥት ጠንካራ የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋም ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ከማገዝ አንጻር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና እጅጉን ከፍተኛ መሆኑን በማመን የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ አድርጓል።
በዚህ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ሀገር በቀልም ሆኑ አለም-አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በልማት፣ በዴሞክራሲ፣ በፍትሕና በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ የሚደርጉት አስተዋፅኦ በኢትዮጵያ እየጎላ መምጣቱን ገልፀዋል። ለዚህ ተሳትፎ ማደግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ሚና ከፍ ያለ መሆኑንም አንስተዋል።
ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ስር ነቀል የተቋም ማሻሻያ በማድረግ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ሚናቸውን የሚያጎሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ወደ ተግባር ስራ እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የተጫወተው ሚና የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከተቋቋሙበት መሠረታዊ ዓላማ ውጪ የሀገርንና የህዝቦችን ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ላይ እየወሰዳቸው ያለው የቁጥጥርና የክትትል ስራዎች መልካም መሆኑን አንስተው ይበልጡንም ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል። የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ከማድረግ አንጻር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል። ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር የሚሰራ ከመሆኑ አንጻር ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ጋር በቀንጅት በመሥራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በኢትዮጵያ የማጠናከር ስራዎችን መሥራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በዚህ የሪፎርም ስራ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ከኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የከፍተኛ አድናቆት የክብር ሽልማት በማግኘቱ እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉ ሲሆን ይህም የተቋሙን ወቅታዊ ቁመና የሚያሳይና ለበለጠ ጥረትና ስራ የሚያተጋ ሽልማት መሆኑን ጠቅሰዋል። በቆይታቸው በባልሥልጣን መስሪያ ቤት የሚገኙ የስራ ክፍሎችን እንቅስቃሴ የጎበኙ ሲሆን ከስራ ክፍል ኃላፊዎች ጋርም ውይይት አድርገዋል።
ከመርሀ ግብሩ ጎን ለጎን የማንበብ ባህልን ለማዳበር በመስሪያቤቱ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን የተመለከቱ ሲሆን የተቋም ግንባታ ሂደትን ስኬታማ ለማድረግ በእውቀትና በአመላከከት የላቀ የሰው ኃይል ማፍራት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አውስተው ባለሥልጣን መስሪያቤቱ የቤተመፅሐፍት አገልግሎት ለሰራተኞች መስጠት መጀመሩና የንባብ ባህል እንዲዳብር ጥረት መደረጉን አድንቀው ይህ የንባብ ባህል ወደ ሌሎች ተቋማት መስፋትና እንደ ምሳሌ መወሰድ እንደሚገባው ጠቅሰዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ስራዎችን ውጤታማ ማድረግ ያስችለው ዘንድ ለባለሥልጣን መስሪያቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።