የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የፍልሰት ተጎጂዎችንና ተጋላጭ ፍልሰተኞችን ለመጠበቅና ለመደገፍ የተዘረጋዉ የብሔራዊ የፍልሰት ተጎጂዎች ቅብብሎሽ ሥርዓት ዓብይ ኮሚቴ ሁለተኛዉ ስብሰባ ትላንትና በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብረሃም አያሌው ባስተላለፉት መልዕክት የፍልሰት ተጎጂዎች ቅብብሎሽ ስርዓት መዘርጋቱ ተጎጂዎችን ለመደገፍ እንዲሁም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ፍልሰትን በመከላከል ረገድ ጉልህ ድርሻ የሚያበረክት በመሆኑ አብይ ኮሚቴው ይሄንን ወሳኝ የሆነ የስራ ድርሻና ከፍተኛ ኃላፊነት በመገንዘብ በቀጣይነት በሚኖሩት ተግባራት ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲደርግ ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በመድረኩም ብሔራዊ የፍልሰት ተጎጂዎች ቅብብሎሽ ስርዓት ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ በፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ቡድን መሪ በሆኑት አቶ አቤል ገ/እግዚአብሄር ገለፃ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት እንደተገለፀው ዜጎች በድንበር አቋርጠው ከሀገር ሲወጡም ሆነ ወደ ሀገር ሲመለሱ እያጋጠሟቸው ያሉትን የተለያዩ ችግሮች ለመቅረፍና የተጎጂዎችን መብት በመጠበቅ ሴቶች፣ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞችን ማዕከል ያደረገ ድጋፍ በማድረግ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለማበጀት እንዲረዳ ብሔራዊ የፍልሰት ተጎጂዎች ቅብብሎሽ ስርዓት መዘጋጀቱን አውስተዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ህገወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የሚረዱ ብሔራዊ ምክር ቤት ከማቋቋም ጀምሮ የትብብር ግብረ ኃይል በማቋቋም በሰዎች መነገድና በህገወጥ መንገድ ከሀገር የማሶጣት ወንጀል ላይ የተሰማሩ አካላትን በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራን ቢያከናውንም ከፍልሰት ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ዘርፈ ብዙ ችግር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማሰቀረት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ከፍልሰት ጋር ተያይዞ የተቀናጀ ምላሽ መስጠጥ አስፈላጊ በመሆኑ በፍልሰት ውስጥ ለሚያልፉ ዜጎች ጥበቃ ከማድረግና ድጋፍ ከማመቻቸት አንፃር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቅብብል የሚሰሯቸውን ተግባራት በማካተት ብሔራዊ የፍልሰት ተጎጂዎች ቅብብሎሽ ስርዓት መዘጋጀቱ ተመላክቷል፡፡
በተያያዘም በመድረኩ በቅብብል ስርዓት መመሪያው መሠረት ለፍልሰት ተጎጂዎች የጤና፣ የስነልቦና እና የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን በየደረጃው በመስጠት ወጥ የሆነ የድጋፍና ክትትል ስራዎች የሚከናወኑበት አቅጣጫ ተመላክቷል፤ በዚህም በቀጣይ 3 አመታት ማለትም ከ 20017 እስከ 2019 እንዲሁም በቀሪዉ 6 ወራት ውስጥ የሚከናወኑ በቀጣይነት የፍልሰት ተጎጂዎችን በፌደራል እና በተለያዩ ክልሎች ደረጃ የቅብብል ስርዓቱ ተግባራዊ የሚደረግበት ፍኖተ ካርታ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ፤ በስብሰባው ተካፋዮች አማካኝነት ፍኖተ ካርታው ሊያካትታቸው የሚገቡ በሚል ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ ከተሳተፉትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የአብይ ኮሞቴው አባላት መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ ቤት፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጤና ሚኒስቴር፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ሲቪል ማህበራት ግብዓት ከሰጡበት በኋላ የትግበራ ነጥቦችን እና ቀጣይ አቅጣጫ በመሰጠት መድረኩ ተጠናቋል ፡፡