"ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የቆየ እና የበለፀገ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት ባለቤት ናት" ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃን

"Ethiopia Possesses a Long-Standing and Rich Traditional Conflict Resolution System" - Honorable Minister of State Dr. Ermias Yemanebirhan

ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ይህን ያሉት የፍትሕ ሚኒስቴር ከአይ ኤስ ኤስ (Institute for security studies) ጋር በመተባበር “ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ለሰላም ግንባታ እና ለብሔራዊ ፍትሕ” በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጁት የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ነው።

ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የቆየና የበለፀገ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ባለቤት መሆኗን የገለፁት ክቡር ሚኒስቴር ዲኤታው እነዚህን ስርአቶች ማኅበራዊ አንድነትን በማስጠበቅ፣ የፍትሕ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ብሎም በሰለም አብሮ ለመኖር አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር በኩል አይተኬ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ስርአቶቹንም ዘላቂ ለማድረግና ለመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ደጋፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ማበረታታትና አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ እንደሚገባ ያከሉት ሚኒስትር ዲኤታው ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ መድረኮች እጅጉን አስፈላጊ መሆናቸውን አፅንኦት በመስጠት ፈጣን ፍትሃዊና ባህላዊ ጠቀሜታ ያለው ፍትሕ ለመስጠት ሲታሰብ በፍትሕ ዘርፉ ለሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች በባህላዊ ግጭት አፈታት መርሆዎች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማዳበር ሥልጠናው መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

አያይዘውም በአገር አቀፍ ደረጃ በፍትሕ ዘርፉ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ለማምጣት የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ፍኖተ ካርታ በመተግበር ላይ መሆኑን እና በዚህ ፍኖተ ካርታ ከተካተቱ አምዶች ውስጥ የመሰረተ ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ አንደኛው መሆኑን አስታውሰው ይህንን ለማሳካትም በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የዛሬውን ጨምሮ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የ Institute for security studies (አይ ኤስ ኤስ) ሪጅናል ዳይሬክተር ዶ/ር ፓሊ ሳይመን በበኩላቸው ተቋማቸው ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ በሽግግር ፍትሕ፣ በአቅም ግንባታ ስራዎች እና በሌሎች ተያያዥ ተግባራት በጋራ እንደሚሰራና ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ሥልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቆይታውም የባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት መርሆዎች እና አጠቃላይ ይዘት፣ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት በኢትዮጵያ በመደበኛና ባህላዊ ፍትሕ ሥርዓት መካከል ያለው ትስስር ብሎም የመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕን አስመልክቶ የፍትሕ ሚኒስቴር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት፣ባህላዊ የፍትሕ አሰጣጥ መሠረታዊ ሃሳቦች፣ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በተለይም ባህልንና ሰብዓዊ መብትን ባማከለ መልኩ አገልግሎት በሚሰጡበት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ ሲሆን በሥልጠናውም የፌደራልና የክልል ፍትሕ ቢሮ ዓቃቢያነ ሕግ፣ የፍርድ ቤት ዳኞች፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

Tagged Under: and healthcare administration and control authority arra (agency for refugees and returnees affairs) birhan conflict Conflict Resolution danish institute for human rights dr. dr. ermias yemaneberhan dr. ermias yemanebirhan ecu ermias ermias yemanebirhan ict institute itu Law Enforcement minister minister of state officer Police res resolution Security standing state studies system traditional Traditional Conflict Resolution yemanebirhan
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች