በኢትዮጵያና በኮሎምቢያ መካከል ትኩረቱን የሽግግር ፍትሕ እና የሰላም ባህል ላይ ያደረገ ዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን በዚሁ ወቅት ሁለቱ አገራት ያላቸውን ልምድ በማጋራት የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።
የሰላም እጦት ጉዳይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ተግዳሮት እየሆነ ያለ ጉዳይ መሆኑ እና ለዚህም ሁሉም አካላት ሰላምን ባህል ለማድረግ በየ ጊዜው መሰል የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት መነጋገር እንዳለባቸው የተገለፀ ሲሆን አገራት በተናጠል ከሚያከናውኗቸው ተግባራት በተጨማሪ በጋራና በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ተመላክቷል።
በተጨማሪም የሽግግር ፍትሕ በመተግበር ሂደት ውስጥ ኮሎምቢያ የተጓዘችበት መንገድ እና የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ የሚገኙ በባህሪ ተቀራራቢ በመሆናቸው የሁለቱን ሀገራት ልምድ ለመቀመር የሚያስችል የልምድ ልውውጦች የሚኖራቸውን ጠቀሜታ የጎላ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ በኩል፣ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም የግብረ ሠናይ ድርጅቶች ሚና በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ገለጻ የቀረበ ሲሆን በኮሎምቢያ በኩል እንዲሁ የሰላም ባህልና የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ዙሪያ ሰፋፊ ማብራሪያዎች ቀርበው ውይይቶች ተካሂደዋል።
ኮንፈረንሱን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ በኢትዬጵያ የኮሎምቢያ ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማህበር በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን ፓሊሲ አውጭዎች፣ ዲፕሎማት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት ተወካዬች እና ሌሎች የዘርፉ ምሁራን ተሳትፈውበታል።