በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጥብቅና ፍቃድ አስተዳደር እና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አማካኝነት በፌደራል ጠበቆች እና የጥብቅና ድርጅቶች ስለሚሰጥ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሥርዓት ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል፡፡
መድረኩን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ እያሱ ቀለሜ እንደተናገሩት በጠበቆች የሚሰጠው የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ከበፊትም ጀምሮ በነበሩት ህጎች ሲሰራበት የነበረ ቢሆንም ማስፈጸሚያ ዝርዝር መመሪያ ባለመኖሩ ምክንያት የአገልግሎቱ ምንነት፣ ከአገልግሎቱ ጋር የተያያዙ መብትና ግዴታዎች ላይ እንዲሁም አጠቃላይ ወሰኑ ላይ የግንዛቤ እና የአረዳድ ውስንነቶች እንደሚታዩ ጠቁመው፤ በጠበቆች የሚሰጠው ነጻ የሕግ ድጋፍ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ከተደረገ የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
ሃላፊው አክለውም ከዚህ ቀደም ረቂቅ መመሪያው ለሕዝብ አሰተያየት ክፍት ተደርጎ እንደነበረ አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ከሚባሉ ባለድርሻ አካላት ግብዓት ለመሰብሰብ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የጥብቅና ፍቃድ አስተዳደርና ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ነስርያ ሱልጣን በበኩላቸው ጠበቃ የማቆም አቀም የሌለው ዜጋ በምን መስፈርት መለየት ይኖርበታል፤ የጠበቆች ክትትል ሂደት ምን መምሰል አለበት እንዲሁም ጠበቃው በአመቱ ውስጥ ያከናወነውን የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በሚመለከት ሪፖርት የማቅረብ ሂደቱ ምን መሆን ይኖርበታል በሚሉ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል በማስፈለጉ ምክንያት መመሪያው መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
መመሪያው በዋናነት የጠበቆችና የጥብቅና ሙያ ድርጅቶች የሚሰጡትን አገልግሎት ግልፅ፣ ፍትሀዊ እና ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ማስቻል ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ የጠበቆችና የጥብቅና ሙያ ድርጅቶች እንዲሁም ተጠቃሚ ዜጎች ያላቸውን መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ የማድረግ ዓላማዎች እንዳሉት ተመላክቷዋል፡፡
የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ ላይ ጠበቆች፣ የጥብቅና ድርጅት ተወካዮች፣ የፌዴራል ጠበቆች ማህበር ተወካዮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ረቂቅ መመሪያውን ለማዳበር የሚረዱ አስተያየቶች ተሰብሰበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡