በህክምና ቸልተኝነት በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የህክምና ባለሙያዎቸ ኮሚቴ ውሳኔ መዘግየት በወንጀል ምርምራ ሂደት ላይ እያስከተለ ባለው ተጽዕኖ እና መፍትሄዎቹ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

Discussion Held on the Impact of Delays in Medical Professionals Committee Decisions on Criminal Investigations of Medical Negligence and Potential Solutions

የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በህክምና ቸልተኝነት በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የህክምና ባለሙያዎቸ ኮሚቴ ውሳኔ መዘግየት በወንጀል ምርምራ ሂደት በሚያስከትለው ተጽዕኖ እና መፍትሄዎቹ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው እንደተናገሩት የዛሬው የውይይት መድረክ ከህክምና ስህተት ጋር በተያያዘ በቸልተኝነት ከሚፈጸሙ የግድያ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በስነ-ምግባር ኮሚቴው በሚሰጡ ማስረጃዎች ዙሪያ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ውይይት መደረጉ የፍትሕ ተቋማት ከጤና ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን በአለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እና በሀገራችን ህገ-መንግሥት ከፍተኛ ጥበቃ የተደረገላቸውን የአካል ደኅንነትና በህይወት የመኖር መብቶች ማስከበር ያስችላል ብለዋል፡፡

የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት የመንግሥት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም የሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚውና የዳኝነት አካሉ የተናጠል እና የወል ግዴታ ተጥሎባቸዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ አንጻር በተለይም ፍትሕ ሚኒስቴርና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተለየ ኃላፊነት አላቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታ የፖሊስና የጸጥታ ሀይሉም እነዚህ መብቶች እንዲከክበሩ፣ ወንጀል እንዳይፈጸም አስቀድሞ ከመከላከል ጀምሮ ተፈጽሞ ሲገኝም አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ የመጀመሪያ ስራቸው ነው ሲሉ ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው አክለዋል፡፡

ከጤና ሚኒስቴር አንጻርም የተሟላ የጤና አገልግሎት በማቅረብ ዜጎች የአካል ደህንነታቸው እንዲጠበቅ በህይወት የመኖር መብታቸው እንዲከበር ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው ይህ የጤና አገልግሎት ደግሞ የሞያ ስነ-ምግባሩን በጠበቀ መልኩ ካልተሰጠ የራሱ የሆነ ችግር ይዞ በመምጣት ዜጎችን ለአካል ጉዳትና ለሞት ይዳርጋል፤ ስለዚህ አስቀድሞ የሞያ ስነ-ምግባሩ ላይ መከላከል መሥራት ወሳኝ መሆኑን አበክረው አንስተዋል፡፡

ወንጀሎች በቸልተኝነት ተፈጽመው ሲገኙ የህክምና የስነ-ምግባር ኮሚቴው ፍጹም በሆነ እና የሞያ ስነምግባርን ባከበረ መልኩ ማስረጃዎችን አጣርቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይጠበቅበታል ተብሏል።

በጤና ሚኒስቴር እና በፍትሕ ሚኒስቴር አጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ከዛ አንጻር በየተቋማቱ የተሰሩ የማሻሻያ ስራዎች ቢኖሩም ከህክምና ስህተትና በቸልተኝነት ከሚፈጸሙ የግድያ ወንጀሎች የስነ-ምግባር ኮሚቴዎች ከሚሰጡት አስተያየት አንጻር በተለያዩ ጊዚያች ችግሮች እንደሚነሱ ያወሱት ሚንስትር ዴኤታው አንዱና ዋነኛው ማስረጃዎቹ ወቅቱን ጠጥብቀው ባለመቅረባቸው የወንጀል ምርመራውንነና የፍትሕ ስርዓቱን ከማዘግየት ባሻገር ማስረጃዎችን በትኩሱ ለማግኝት እድል አይሰጥም ይህ ደግሞ ሌላ ችግር በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ያመጣል ብለዋል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጹሁፍ አዘጋጅቷል የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎች ዘርፍም ለዚህ የተለየ ትኩረት በመስጠት የምርመራና የክስ ማንዋል ማዘጋጀቱን ያነሱት ሚኒስትር ዴዔታው ይህ በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ውይይት ተደርጎበት በቀጣይ የ2016 በጀት ዓመት ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረው የመድረኩን መከፈት አብስረው ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡

የሚኒስቴር ዴኤታውን ንግግር ተከትሎ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በኩል የተዘጋጀው የውይይት መነሻ ጹሁፎች በአቅራቢዎች በኩል ለመድረኩ ተሳታፊዎች የቀረበ ሲሆን፤ የመነሻ ጥናታዊ ጹሁፉ ዓላማም ከህክምና ስህተት ጋር በተያያዘ የሰው ህይወት ባለፈባቸው የወንጀል ምርመራ መዛግብት የህክምና የስነ-ምግባር ኮሚቴ የሙያ አስተያየት ያለውን ፋይዳ እና የአስተያየት አለመምጣት ፈጣንነና ጥራቱን የጠበቀ ውሳኔ ላለመስጠት ያለውን ተጽዕኖ በማመላከት የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ማስቻል መሆኑን በቀረበው የመነሻ ሰነድ ላይ ተመላክቷል፡፡

የሙያ አስተያየት በመስጠት ሂደት የሚኖሩ መዘግየቶች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የሚያስከትሏቸው አሉታዊ ውጤቶች ምን ምን እንደሆኑ፣ እና የመፍትሄ ሀሳቦቹም ጭምር በመነሻ ሰነዱ ላይ ተካቶ ቀርቧል፡፡

በመጨረሻም በክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ አለምአነንተ አግደው እና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ጽ/ቤት ኃላፊ በሆኑት በአቶ በረከት ማሞ አወያይነት በቀረበው መነሻ ሰነድ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በመድረኩ ተሳታፊዎች ተነስተው የማጠቃለያ ሀሳብ በሚኒስቴር ዴዔታው ተሰጥቶ የዕለቱ መርኃ ግብር ተጠናቋል፡፡

በመድረኩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ከህክምና ስነ-ምግባር ኮሚቴዎች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጡ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡

Tagged Under: Case Backlog committee criminal Criminal Investigation Criminal Procedure decisions ethics Health Human Rights Violations Investigation Justice Justice System legal Legal Proceedings malpractice medical medical malpractice medical negligence ministry ministry of health negligence policy recommendations professional misconduct Right to Life Stakeholder Consultation system
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች