የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን፣ የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ ፣የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ላይ ለሚፈጸም ጥቃት ምላሽ ለመስጠት የሚቋቋሙ የተቀናጀ ፍትሕና እንክብካቤ ማዕከላትን ማጠናከርና ማስፋፋትን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሀን የውይይት መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከልን ምላሽ ለመስጠት የፍትሕና እንክብካቤ ማዕከላትን ማጠናከር፣ ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻል እና ቅንጅታዊ አሰራሩን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የፍትሕና እንክብካቤ ማዕከላቱ ያሉበትን ሁኔታ በመረዳት የተሸለ አገልግሎት እንዲሰጡ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
የሴቶች፣ ሕፃናትና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አለምኔ የተቀናጀ የአንድ ማዕከላት አገልግሎት አስፈላጊነት፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አስፈላጊነትና ጠቀሜታ፣ በማዕከላት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚዳስስ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ አቅርበዋል፡፡
ዳይሬክተሯ በአገር ደረጃ 72 ያህል ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ እና ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ በፊዴራል ደረጃ (አዲስ አበባና ድሬደዋ) የሚገኙ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን በአዲስ አበባ ያሉት የጋንዲ፣ ዳግማዊ ሚኒሊክ፣ ጥሩነሽ ቤጅንግ እና አበበች ጎበና ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ አያይዘውም እነዚህ ማዕከላት በርካታ ተጎጅዎችን እያገለገሉ ቢሆንም የሰው ኃይልና የግብዓት እጥረት ያለባቸው መሆኑ እና አንዳንድ ስራዎች አሠራር ያልተዘረጋላቸው መሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር መፍጠሩን አንስተዋል፡፡
የፍትሕና እንክብካቤ ማዕከላት የተጎጅዎችን እንግልት እና ተደጋጋሚ ጉዳት የሚቀንሱ በመሆናቸው አሁን በስራ ላይ ያሉትን ማዕከላት ማጠናከር እንዲሁም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተያያዘም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት በሚፈለገው ልክ አለመሆን እና ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እና መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡ ከተደራሽነት አንጻርም የታሰቡ የማስፋፊያ እቅዶችን ውጤታማ ለማድረግ የበላይ አመራሩ ድጋፍ፣ የጤና አገልግሎት ያለክፍያ አሠራር ተግባራዊነት ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት፣ የአሠራር ስርዐት የሌላቸው ጉዳዮች ላይም የውሳኔ ሀሳብ እንዲሰጥበት፣ ከግብዐትና ሰው ኃይል ማሟላት ጋር ተያይዛ የበላይ አመራሩ አቅጣጫ እንዲሰጥባቸው የቀረቡ ሀሳቦች ናቸው፡፡
የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ፍሬህይወት በበኩላቸው ከጤና አገልግሎት አንጻር እየተከናውኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው ማዕከላቱን ከማጠናከር እና ተደራሽ ከማደረግ አንጻር መከናወን ያለባቸው ተግባራትና የባለድርሻ አካላት ሚና በዝርዝር ተለይቶ መዘጋጀት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ክብርት የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ እስካሁን ባለው ሂደት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግና ለማጠናከር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አስረድተው በቀጣይ በተለይ አሠራር ሊዘረጋላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በመለየት አሠራር መዘርጋትና ቅንጅታዊ አሰራሩን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አውስተዋል፡፡
በአጠቃላይ አሁን ላይ አግልግሎት እየሰጡ ያሉ ማእከላት የሚሰጡትን አግልግሎት ጥራት ለማሻሻል እና የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ሚና እና ማዕከላቱን ተደራሽ ከማደረግ አንጻር መከናወን ያለባቸው ተግባረት ላይ ውይይት የተደረገ ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስት ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሀን በየተቋማቱ በቀጣይ መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡