የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች እርስ በርሳቸው ባልተግባቡበት የፍትሐ ብሄር ጉዳይ ዙሪያ ፍትሕ ሚኒስቴር ውሳኔ የሚሰጥበት የሥነ ስርዓት ረቂቅ መመሪያ ላይ ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሕግ ክፍል ኃላፊዎች ጋር መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ውይይት ተደርጓል።
ውይይቱን የመሩት የፍትሐ ብሄር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት አቶ ሔኖክ ተስፋዬ እንደገለጹት የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣን እና ኃላፊነት ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40(2)(ሀ) መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች እርስ በርሳቸው ባልተግባቡበት የፍትሐ ብሄር ጉዳይ ዙሪያ ውሳኔ እንዲሰጥ የተሰጠውን ሥልጣን ተግባራዊ ለማድረግ ረቂቅ የሥነ ስርዓት መመሪያ ተዘጋጅቷል ብለዋል። ዳይሬክተር ጄነራሉ ረቂቅ የሥነ ስርዓት መመሪያው የተዘጋጀበትን ዓላማ ሲያስረዱ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እርስ በርስ በመካሰስ የሚፈጠርን አላስፈላጊ የጊዜ እና የገንዘብ ብክነት ለማስቀረት እና በተቋቋሙለት ዓላማ ላይ እንዲያተኩሩ እና ኃላፊነቶቻቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ ማገዝ ነው ብለዋል። እርስ በርስ የሚኖራቸውም ግንኙነት የባላንጣነት ሳይሆን በመተባበር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከማስቻልም በላይ አለመግባባት ውስጥ የገቡበት ጉዳይ በመግባባት ተፈትቶ ለታለመለት ህዝባዊ አገልግሎት እንዲውል ያስችላል ብለዋል። በተጨማሪም መመሪያው ተቋማት እርስ በርስ በሚኖራቸው አለመግባባት መነሻነት ፍርድ ቤት ይደረግ የነበረውን ክርክር በማስቀረት የፍርድ ቤቶችን የስራ ጫና ማቃለል እና ዜጎችም የተቀላጠፈ ፍትሕ እንዲያገኙ በማድረግ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጡን ያግዛል ብለዋል።
የረቂቅ የሥነ ስርዓት መመሪያው መዘጋጀት በመንግሥት ተቋማት መካከል የተፈጠረን የፍትሐ ብሄር አለመግባባት በመመልከት ውሳኔ የሚሰጥበትን ሂደት ለመደንገግ ያለመ ሲሆን አሰራሩ ግልጽነት ያለው እንዲሆን የሚያስችል እና በሂደቱ ተሳታፊ የሚሆኑት ሰዎች የሚኖርባቸውን ተጠያቂነት የማመልከት ሚናን ይጫወታል።
የመንግሥት ተቋማት የሕግ ክፍል ኃላፊዎች የተቋሞቻቸውን የፍትሐ ብሄር ጉዳይ በመከታተል ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው እንደመሆኑ እና በመመሪያው ትግበራ ሂደት ዋነኞቹ ተዋናዮች እንደመሆናቸው በውይይት መድረኩ ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል። በውይይቱም ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎች በማንሳት እና አስተያየቶችን በመለገስ ረቂቁን የበለጠ ለማዳበር የሚረዳ ግብዓት ሰጥተዋል።
ዳይሬክተር ጄነራሉ እንደገለጹት በተሰጠው ግብዓት ረቂቁን በማዳበር እና የሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላትም አስተያየት እንዲሰጡበት በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጽድቆ ወደስራ እንዲገባ ይደረጋል።