በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የህክምና እና ተያያዥ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የምርመራና ክስ ማኑዋልን ለማስተዋወቅ የሚያስችል የውይይት መድረክ የሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራል ተቋማት ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሄደ፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ፣ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ አዲስ ጌትነት መድረኩን ሲከፍቱ ማንኛውም ሰው የማይደፈርና የማይገሰስ ሰብዓዊ መብት እንዳለው እና ይህም ጤናው ተጠብቆ በህይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት እና የነጻነት መብትን እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡
አቶ አዲስ አያይዘውም ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ቀዳሚ ግዴታ በመንግሥት ላይ የተጣለ በመሆኑ መንግሥት የጤና መብትን ለማስከበር የሚያግዙ ፖሊሲና ሕጎችን ማውጣት የሚጠበቅበት ከመሆኑም በላይ በሕይወት ወይም በአካል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የጤና አገልግሎቱን የማስፋት፣ የጤና አገልግሎት የሚሰጥበትን ደረጃ (ስታንዳርድ) የማውጣት፣ በጥራት የመስጠትና በዚህ ረገድ እየደረሰ ካለ አደጋ ማንኛውንም ሰው የመጠበቅ ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ መጔደል የተነሳ በሰው ሕይወት እና ሌሎች መብቶች ላይ የመብት ጥሰት እንዳይደርስ የመከላከል፣ መብት ተጥሶ ከተገኘም አስፈላጊውን ምርመራ እንዲከናወን እና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ አዲስ በገለጻቸው ማኑዋሉ በህክምና እና ተያያዥ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመመርመርና ለመክሰስ የሚከናወኑ ተግባራትን የበለጠ ለማሳለጥ እና ውጤታማ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን አንስተው የማኑዋሉ ወጥቶ ስራ ላይ መዋል ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በጤናው ዘርፍ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በአግባቡ ለመመርመርና ክስ ለመመስረት የተሻለ እይታ እና ወጥነት ያለው አሠራር እንዲኖር ያደርጋል፤ ይህም በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ አጥፊዎች ከንፁሃን የሚለዩበትን እና በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፤ ከዚህም ባሻገር የጤና ባለሙያዎች የሙያ ነጻነታቸውን ጠብቀው እና የሙያ ስነ-ምግባሩን አክብረው እንዲሰሩ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል ።
የክልልና የፌዴራል ተቋማት አመራሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት መድረክ ማኑዋሉን ማስተዋወቅ ያስፈለገው የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ አስፈላጊ ስለሆነ ተቋማቱ ማኑዋሉን አውቀውት እና በባለቤትነት ወስደው እንዲተገብሩት ለማድረግ መሆኑን አቶ አዲስ ጠቁመዋል፡፡ በመድረኩ ማኑዋሉን ለማዘጋጀት የተሰራው የዳሰሳ ጥናት እና ማኑዋሉ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።