የጠበቆች የታክስ አከፋፈልን በተመለከተ የሚነሱ ችግሮችን ለማጥናት የተቋቋመው ኮሚቴ ስራውን ጀመረ

Committee Established to Study Issues Related to Lawyers' Tax Payment Begins Work

የጠበቆች የታክስ አከፋፈልን በተመለከተ የሚነሱ ችግሮችን ለማጥናት ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከጠበቆች ማህበር ተውጣጥቶ የተቋቋመው ኮሚቴ በዛሬው ዕለት በፍትሕ ሚኒስቴር ለመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ባቀረበው ሪፖርት ስራውን መጀመሩን ገልጿል::

የጥናቱ ዋና ዓላማ ጠበቆች በየጊዜዉ በግብር እና ታክስ መክፈያ ወቅት እያጋጠማቸዉ ላለዉ ችግርና ወጥነት የሌለዉ የታክስ አከፋፈል ስርዓት መነሻ ምክንያቶቹን በማጥናት ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃ ሊሆኑ የሚችሉ ምክረ-ሀሳቦችን ማቅረብ እንዲያስችል መሆኑን በቀረበው የስራ ማስጀመሪያ መርኃ-ግብር ሪፖርት ላይ ተመላክቷል፡፡

ጠበቆች የሙያ አገልግሎታቸውን መሠረት በማድረግ በሚያገኙት ገቢ ላይ ሊከፍሉት የሚገባውን የገቢ ግብርና ታክስ፣ የአከፋፈል ምጣኔና የአከፋፈል ስርአቱን በተመለከተ በተለይ ከ2004 ዓ.ም አንስቶ አከራካሪ ጉዳዮች ሲነሱበት ቆይቷል፡፡ በወቅቱ ከግብር እና ታክስ አከፋፈል ጋር በተያያዘ ጠበቆች እየገጠማቸው የነበረውን ችግር በተለይም በርካታ ጠበቆችን የሂሳብ መዝገብ ካልያዛችሁ አትስተናገዱም፣ በቁርጥ ግብር አናስተናግድም ስለተባሉ በጥናት ላይ ተመስርቶ ዘላቂ መፍትሔ እስከሚሰጠው ድረስ በነበረበት አንዲቀጥል ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የጥናት ቡድኑ በሪፖርቱ ላይ ጥናቱን እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ አጠናቆ እንደሚያስረክብ በሪፖርቱ ላይ አስቀምጧል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ላይ የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ከተደረገ በኋላ በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት አቶ አለማንተ አግደው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለጥናት ቡድኑ አብራርተው የዕለቱ መርኃ-ግብር ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: administration association compliance dispute finance Fiscal Policy Income Income Tax Lawyers legal Legal Profession ministry Ministry of Finance payment Policy profession report Revenue revenue collection Tax tax administration tax compliance Tax Payment tax policy tax reform taxation
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች