በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የክልል ጉዳዮች ዳሬክቶሬት አስተባባሪነት የተዘጋጀና የለሙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ላይ ያተኮረ የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሂዷል፡፡
ከአፋር ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ቤ/ጉሙዝ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ምዕራብ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮዎች የተወጣጡ የወንጀል ጉዳዮች፣ የፍትሀብሔር አስተዳደር ጉዳዮች፣ የአይሲቲ እና የዐቃቤያን ሕግ አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ሃላፊዎችና ዳይሬክተሮች የተሳተፉበትን የልምድ ልውውጥ መድረክ ያስጀመሩት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ አማካሪ አቶ አማኑኤል ታደሰ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ስድስት አመታት መንግሥት ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል አንደኛው ቴክኖሎጂ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የዜጎችን መብት የሚገድቡና የአገልግሎት አሰጣጡንም የሚያስተጓጉሉ አሰራሮችን በማስቀረት ወጥ እና የተደራጀ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ሀገር አቀፍ የትራንስፎርሜሽ እቅድ ተቀርፆ ትግበራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አማካሪው አያይዘውም ቴክኖሎጂን ለዘርፉ እንዲመች አድርጎ በመጠቀም በክልል ደረጃ የሚከናወኑ ተግባራትን ማገዝ፣ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ መስጠት እንዲሁም ከተለመደው የማኑዋል አሠራር ልማድ መውጣት ተገቢ ስለሆነ ለዚህ የሚያግዙ የልምድ ልውውጥ መድረኮችን አዘጋጅቶ የእውቀት ሽግግር በማድረግ አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቀጥሎ ቴክኖሎጂን መጠቀም መቻል በጥምረት የመሥራት አጋጣሚን እንደሚፈጥር የተናገሩት ደግሞ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቤ ሕግ አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታነህ ሀብታሙ በበኩላቸው በፍትሕ ዘርፉ ውስጥ በፌዴራል እና ክልል ቢሮዎች የሚገኙ አካላት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣ እና ስራን ቀላል በሆነ መንገድ ለማከናወን እንዲችሉ በማድረግ ረገድ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦን እያበረከተ መሆኑን አመላክተው፤ በዚህም በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን የባለሙያ ፍልሰት ለመቀነስ እንዲረዳ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጋራ የሆነ የአሠራር ስርዓትን በመዘርጋት የተናበበ የሠራተኛ ቅጥር መፈፀም እንደሚቻል፤ ከዚህ በተጨማሪ የባለሙያውን የስራ አፈፃፀም፣ ውጤት፣ ስነምግባር እና ሌሎች ጉዳዮችን የሚያመለክት ዳታን አደራጅቶ በመያዝ በሚያስፈልግበት ጊዜ በቀላሉ መረጃውን መለዋወጥ እንደሚያስችል ገልፀው፤ የልምድ ልውውጥ መድረኩ መዘጋጀቱ በቀጣይ የሚኖሩ ስራዎችን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ወጥነት ባለው መንገድ ለማከናወን የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ቀርበው በባለሙያዎች ገለፃ የተደረገባቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፕላት ፎርሞች አስመልክተው ንግግር ያደረጉት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና መዝገብ ቤት አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ፀጋዬ አማረ በበኩላቸው እስካሁን በነበረው ጊዜ የፍትሕ ሚኒስቴር በግሉ እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን 22 ያህል ሲስተሞችን ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ የወንጀል መረጃ ምዝገባ ስርዓት፣ የዐቃቤ ሕግ የስራ አፈፃፀም መመዘኛና ውጤት መስጫ ፣ የስራ መከታተያ ዳሽቦርድ ሲስተም እንዲሁም ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የተዘጋጀና ለሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግብረ መልስ መመዝገቢያ የሚሆኑ ሲስተሞች መኖራቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡ በቀጣይም ለክልል የፍትሕ ቢሮዎች ለስራቸው አጋዥ ተደርገው የተዘጋጁትን ሰባት ያህል የለሙ ሲስተሞች ወስደው በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ የሚረዱ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎች የሚደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የልምድ ልውውጥ መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ፍትሕ ሚኒስቴር ለስራ አመቺ የሆኑ ሲስተሞችን ማዘጋጁቱና በየጊዜው ለክልሎች የሚያደርገው እገዛ አበረታች መሆኑን ገልፀው፤ ለወደ ፊት በሀገር ደረጃ ወጥነት ያለው የፍትሕ ዘርፍ እንዲኖር ከወዲሁ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ክልሎች ለቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዲችሉ ማድረግ ሲቻል ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ቀጥሎም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የክልል ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ዳሬክተር የሆኑት አቶ አበራ አሰፋ ለዘርፉ የተዘጋጀውን የቴክኖሎጂ ፕሮግራም ለመምራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀላፊነቱን ወስዶ የክልሎችን የባለሙያ አቅም በሥልጠና በማጎልበት እንዲሁም ግብዓቶችን በማቅረብ ተከታታይ የሆነ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀው፤ ክልሎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጣቸው እንዲሻሻል በቁርጠኝነት ለመሥራት ከወዲሁ መዘጋጀት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመጨረሻም ለዕለቱ በተያዘው የማጠቃለያ መርሀ-ግብር መሠረት ተሳታፊዎቹ አይ.ሲቲ. ፓርክ /Wingu Africa Datacenter/ በመገኘት ጉብኝት ካደረጉ በኋላ የልምድ ልውውጥ መድረኩ ተጠናቋል፡፡