በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤት እና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የሚመሩት እና የፍልሰት ተመላሾችን በመደገፍ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው መኖር የሚያስችላቸውን አቅም ለመፍጠር የሚያግዙና በአውሮፓ ህብረት እና በስዊድን መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ የገነዘብ ድጋፍ የሚተገበሩ ሁለት ፕሮጀክቾች ጥር 28/2018 ዓ.ም ይፋ ሆነዋል፡፡
ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በአንድነት ያካተተው የፍልሰት ብሔራዊ የትብብር ጥምረት በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚመጡ የፍልሰት ተመላሾች ከማህበረቡ ጋር ተቀላቅለው መኖር የሚችሉባቸውን አማራጮች የማመቻቸት ተግባራትን በማስተባበር ላይ ይገኛል፡፡
በፕሮጀክቶቹ የማብሰሪያ ሥነ-ስርዓት ላይ እንደተገለፀው ኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ ፍልሰትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ በመቀጠል የፍልሰት ተመላሾችን ወደ ሕብረተሰቡ የማቀላቀል ሥራው አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ጉዳዩን በከፍተኛ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እንዲመራ ከማድረግ ጀምሮ፣ ለፕሮጀክቶች የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች በማሟላት፣ የፍልሰት ተመላሾችን በጊዜያዊ ማቆያዎች ተቀብሎ የመከላከልና የመጠበቅ አገልግሎትን መስጠት፣ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን በወንጀል ሕግ ተጠያቂ የማድረግና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን በማከናወን ረገድ በመንግሥት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት የተገለፀ ሲሆን፤ በቀጣይነትም በፕሮጀክቶቹ የሚተገበሩትን ፍልሰተኞችን በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ሥራዎች ለመምራት፣ በቅርበት ለመከታተልና ሁሉን አካታች ሆነው እንዲተገበሩ ለማድረግ ዝግጁነት መኖሩ ተመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ ሁለቱን ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ 2.4 ቢልዮን ብር የፋይናንስ ድጋፍ መዘጋጀቱና የፕሮጀክቱ አስፈጻሚ አካልም ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) እንደሆነ የታወቀ ሲሆን፤ ድጋፉም ፕሮጀክቶች ስራ ላይ ሲውሉ የፍልሰት ተመላሾችን በዘላቂነት ለማቋቋም፣ ሲመለሱ ተቀብሎ የህክምናና የስነ ልቦ ድጋፎችን ከማድረግ ጀምሮ በእርሻ፣ በዶሮ እርባታ፣ በፕላስቲክ ሪሳይክሊንግ፣ በምርትና አገልግሎት እና ተያያዥነት ባላቸው መስኮች ላይ ተሰማርተው እንዲሰሩ ለማድረግ የሥራ ክህሎት ሥልጠናዎችን ለማዘጋጀትና ተመሳሳይ ተግባራትን ለማከናወን የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡
በማብሰሪያ ሥነ-ሥርዓት መድረኩ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በውይይቱም የፕሮጀክቱ አተገባበር መንግሥት ተመላሽ ዜጎችን ለማቋቋም በአወጣቸው ፖሊሲሰዎች፣ ህጎች እና ፕሮግራሞች ተካቶና ተሰናስሎ የሚተገበር እንደሚሆን ተገልጿል።
በመጨረሻም የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰሎሞን ሶካ፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ሰብሳቢ እንዲሁም የስዊድን አምባሳደር በፕሮጀክት ስምምነት ሰነዶቹ ላይ ፊርማቸውን በማኖር ፕሮጀክቶቹን በይፋ አስጀምረዋል፡፡