በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ እና የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የአውሮፓ ሕብረት የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩን ሪፎርም ለማደርግ ባደረገው ድጋፍ እና በገለልተኛ ከፍተኛ አማካሪ በተዘጋጀ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የተገልጋዮች እርካታ የዳሰሳ እና የማሻሻያ ፍላጎት ልየታ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ፣የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ ፣የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ እና የተቋሙ መካከለኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ይህ ረቂቅ የጥናት ሰነድ እስከዛሬ ሲሰራበት ከነበረው የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ምን ላይ ማተኮር አለብን ? ምን ማሻሻል አለብን? ምን ማስተካከል አለብን? ትኩረታችን ምን ላይ መሆን አለበት? የሚለውን ጉዳይ በተሻለ ሁኔታ የሚያሳይ እንደሆነ ገልፀው በጥናት ሰነዱ ላይ በመወያየት ፣ ግብአት በመስጠት ሰነዱን በማዳበር ለቀጣይ ስራዎች ለመነሻ ጥናት እንዲያገለግል ማስቻል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ እና የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኖህ ታከለ በንግግራቸው የፍትሕ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም የፍትሕ አገልግሎት እንደሚሰጥ አንስተው ተቋሙ የሚሰጠው የፍትሕ አገልግሎት በተገልጋዩ ዘንድ ያለው የእርካታ ደረጃ ምን ይመስላል የሚሉ የአሠራር መመዘኛዎች እና አመላካቾች ላይ ወጥ የሆነ አሠራር ስርኣት እንዳልነበር የጠቀሱት አቶ ኖህ፤በዚህም ምክንያት ያለውን አሠራር ወጥ አድርጎ ለማስኬድ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተገልጋይ ማኅበረሰብ እርካታ ምን ይመስላል? በተገልጋዮች ዘንድ የሚነሱ ችግሮች ምንድን ናቸው?የሚለውን ጥናት በፍትሕ ሴክተር ረዥም አገልግሎትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የ2014ና የ2015 ሙሉ በጀት ዓመት እንዲሁም የ2016 ግማሽ በጀት ዓመት የአገልግሎት እርካታ ደረጃ በጥናት እንዲዳሰሱ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ጥናቱን ያጠኑት ከፍተኛ አማካሪ አቶ ደሳ ቡልቻ በጥናት ሪፖርት ያካተቷቸውን በጥናቱ የተገልጋይ እርካታ ዳሰሳ፣የጥናቱ አካሔድ ፣ ዘዴዎችና መሳሪዎች፣ የተቋሙ ተደራሽነት፣የተቋሙ አገልግሎት አስተማማኝነት፣ የናሙና መጠንና የተሳታፊዎች መረጃ፣ የተገልጋዮች እርካታ ዳሰሳ የጥናት ውጤት፣ የዕምነትና የእርካታ ደረጃ፣ ዝርዝር ተቋማዊ ጉዳዮች፣ ጠንካራና ደካማ አፈጻጸም የታየባቸው የአገልግሎት ጉዳዮች፣ የቅንጅታዊና ትብብራዊ ስራዎች ደረጃ፣ የተለዩ ቁልፍ ክፍተቶችና ውስንነቶች እንዲሁም የቀጣይ ማሻሻያ እርምጃዎችና ምክረ ሀሳቦችን ገለጻ አድርገዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር)፣ አቶ ኖህ ታከለ እና አቶ ደሳ ቡልቻ የቀረበውን የጥናት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት እንዲቀርብ እድል በመስጠት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በቀጣይ እንደዘርፍና እንደ ስራ ክፍል በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮች እንደግብዓት መወሰድ እንዳለበት፣ የተነሱ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና መሻሻል የሚስፈልጋቸውን ደግሞ በማሻሻል ሰነዱ መዳበር እንዳለበት አመላክተዋል። ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡