በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የፍትህ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ለማጠናከር የሚያስችል አህጉራዊ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል

A Regional Conference Is Underway In Addis Ababa Aimed At Ensuring Universal Access To Justice In Africa And Strengthening Traditional Dispute Resolution Mechanism

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን በማጠናከር ሁሉን አቀፍ የፍትህ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ አህጉራዊ ኮንፍራንስ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም “Strengthening Traditional Dispute Resolution for Access to Justice in Africa” በሚል መሪ ቃል በመካሄድ ላይ በሚገኘው በዚህ ኮፍራንስ የፍትሕ ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርዓያ ስላሴ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረትን ጨምሮ ከኢትዮጲያ እና ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የፍትሕ እና ዳኝነት አካላት፤ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፤ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮች ፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡

በኢትዮጲያ ውስጥ በርካታ አለመግባባቶች የሚፈቱት በባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ሲሆን እነዚህ አገልግሎቶች በቅርበት የሚገኙ እና ከማህበረሰቡ ባህል ጋር የተስማሙ በመሆናቸው አዋጭነታቸው እና ተደራሽነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች በአፍሪካ የፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ በተለይም ዘመናዊ የፍትሕ አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ፍትሕን ከማረጋገጥ አንፃር ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም በፍትሕ ሚኒስቴር እና በሚመለከታቸው አካላት ቅንጅት እነዚህ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ የሕግ ማዕቀፍ ተበጅቶላቸው ሚናቸውን የሚወጡበትን ሁኔታ ሲያመቻች የቆየ ቢሆንም ይህ ተግባር ከእኩልነት ከመሰማት መብት እና ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ከሆኑ ወገኖች ጥበቃ ጋር ተያይዞ በሕገ-መንግስቱ ከተቀመጡ መርሆዎች እና ከዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች እና ግዴታዎች አንፃር ለማጣጣምና ከየ ሀገራቱ ልምዶች ለመማማር እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት መካል ከባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓት አንጻር በትብብር መስራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ አህጉራዊ ኮንፈረንስ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

ይህ ኮንፍረንስ በባሕላዊ እና በማኅበረሰብ-ተኮር የግጭት አፈታት ስርዓቶች ረገድ ያሉ የአፍሪካ ምርጥ ተሞክሮዎችን የመለዋወጥ፣ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶችን ከመደበኛው የሕግ ማዕቀፍ ጋር ማቀናጀት የሚቻልባቸውን መንገዶች የመፈለግ፣ በባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ውስጥ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትን እና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን የማበረታታት፣ በቀጣናዊ ትምህርት እና በእውቀት ልውውጥ አማካኝነት በኢትዮጵያ የሚገኙ የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትህ ተነሳሽነቶችን የማጠናከር፣ እና የፍትሕ ሥርዓቶች ዘላቂ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበትን ዘዴዎችን የማፈላለግ ዓላማ ያለው መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በኮንፈረንሱ እንደተመለከተው በርካታ የአፍሪካ አገራት የፍትህ ሥርዓቶች ከተደራሽነት፣ ውጤታማነት እና ሁሉን አቀፍነት አንጻር የሚነሱባቸው ተጠያቂነቶች መኖር፤ ከከተማ ርቀው የሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ የመደበኛ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት ተደራሽነትን ውስን ማድረጉ፣ ፍትሕ ለማግኘት ከፍተኛ ወጪ መኖር፣ የሥነ-ሥርዓት ውስብስብነት እንዲሁም የክሶች መከማቸት ችግሮች መኖራቸው ተጠቅሶ፤ እነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት ፍትሕን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግና ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊደረግበት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ኮንፍራንሱ በዛሬ ዉሎው “ፍትህን ከአካባቢው ማህበረሰብ መዋቅር መገንባት”፣ “ባህላዊ ፍትህን ከሀገራዊ ልማትና ከህግ የበላይነት ስልቶች ጋር ማቀናጀት”፣ “ፍትህን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ማጎልበት”፣ “በባህላዊ ዳኝነት ውስጥ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች እንዲከበሩ ማድረግ”፣ “በባህላዊ የግጭት አፈታት ውስጥ የጾታ እኩልነትን፣ አካታችነትን እና ሰብዓዊ መብቶችን ማረጋገጥ” በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች የአፍሪካ ተሞክሮዎች እና ልምዶች እንዲሁም የየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ፓናል ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች እና ሃሳቦችም ምላሽና ማብራሪያዎች የተሰጡ ሲሆን ልዩልዩ ተሞክሮዎች የታዩበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን በማጠናከር በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የፍትህ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚመከሩበት አህጉራዊ ኮንፍረንስ የፍትሕ አመራሮችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን እንዲሁም በአፍሪካ የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎችን በማገናኘት የእርስ በርስ የልምድ ልውውጦች የሚደረጉበት፣ ማኅበረሰብ-ተኮር የሆነ የፍትሕ ስርዓትን ለማጠናከር የጋራ ትብብር ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡

Tagged Under: 11th east africa international arbitration conference ababa access Access to Justice addis addis ababa addis ababa justice bureau Addis Ababa Science and Technology University addis ababa water and sewerage authority Africa african charter on the rights and welfare of the child conference dispute Dispute Resolution dispute resolution mechanisms ica Justice mechanism mechanisms region Regional res resolution ring strengthening traditional traditional dispute resolution un universal way
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች