በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር አስተባባሪነት “በኢትዮጵያ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች የአሰልጣኞች ስልጠና (Training of Trainers ) ረቂቅ መመሪያ” ላይ የባለሙያዎች ውይይት ተካሂዷል።
የፍትሕ ዘርፍ ባለሙያዎች፣ የዳኝነት አካላት እና በማህበረሰብ ተኮር የፍትሕ ስርዓት ላይ የሚሰሩ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ያሳተፈው የውይይት መድረክ የረቂቅ የመመሪያውን ዋና ዋና ይዘቶች በመገምገም የሽማግሌዎችን፣ የአሰልጣኞችን እና የማህበረሰብ ፍትሕ አስተባባሪዎችን አቅም ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑ ተመላክቷል።
በመድረኩ በተለይም ሕጋዊ ብዝሃነት፣ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ፣ የፆታ እኩልነት፣ ፍትሃዊ የመሰማት ሂደት እና የሪፈራል ስርዓት፣ እንዲሁም በባህላዊ እና መደበኛ የፍትሕ ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት ላይ ሰፊ ሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል።
ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች እሴት በመጠበቅ ከህገ መንግሥታዊ መርሆዎችና ከሰብአዊ መብቶች ጋር ተጣጣሚ የሆነ የፍትሕ ስርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች በእርቅ፣ በማህበራዊ ሰላም እና በፍትሕ ተደራሽነት ላይ ያላቸው አስተዋፅኦ ማጠናከር በሚያስችል ሁኔታ ላይ ግብዓት መስጠት ተችሏል።
ይህ ረቂቅ መመሪያ በኢትዮጵያ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ እና የፍትሕ ሥርዓት ለውጥ ሂደት አካል ሲሆን፣ ለማህበረሰብ ቅርብ፣ ተደራሽ እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የፍትሕ ሥርዓት ለመግንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መሰረት እንደሚሆን ተገልጿል።