የግልግል ዳኝነት ማዕከላት ፈቃድ አሰጣጥ፣ምዝገባ እና ቁጥጥርን አስመልክቶ በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ከፍርድ ቤት፣ጠበቆች፣ከዩኒቨርስቲ ተወካዮች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስትር የፍትሃብሔር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሄኖክ ተስፋዬ በዘርፉ ሲካሄድ በቆየው ሰፊ የለውጥ ስራ ዘመናዊ የግልግል ዳኝነት ሕግ ማውጣት መቻሉ፣የኒውዮርክ ኮንቬንሽን መፈረሙ፣እና በፍርድ ቤቶች ጭምር ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እድገቱን የሚያመላክት መሆኑን በማንሳት እነዚህን በጎ ተግባራት በተሻለ ለማስፋትና ተግባራዊነታቸውንም እውን እንዲሆን ለማስቻል የፍትሕ ሚኒስቴር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝና የግልግል ዳኝነትን በተለይም ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የሶስት አመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በማካተት እየተሰራ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።
ረቂቅ ደንቡን ለማዘጋጀትም ባለፉት አመታት ሰፋ ያለ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱንና በ2016 ዓ.ም በተደረገ የመጀመሪያ ውይይት ከባለሙያዎች የተሰጡ አስተያየቶችን በግብአትነት በማካተት ተጨማሪ ጥናት በማድረግና በማሻሻል ረቂቅ ደንቡን ማዘጋጀት እንደታቸለ ገልፀዋል።
የግልግል ዳኝነት ረቂቅ ደንብን በማዘጋጀት ሂደት የተሰሩ ስራዎችንና አጠቃላይ ደንቡ ላይ ገለፃ ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስትር የፍትሃብሔር ፍትሕ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ንጉሴ ትዕዛዙ የግልግል ዳኝነት አገልግሎት እስካሁን ባለው ሂደት ተቋማዊ ባልሆነ መንገድ ሲመራ የነበረ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ በሚፈለገው ደረጃ የተጓዘ እንዳልነበር አንስተዋል።
በመሆኑም የግልግል ዳኝነት ማዕከላት የሚመራበት ወጥ የሆነ ሕግና ደንብ ማዘጋጀት አስፈላጊነትን ሲያብራሩ በተለይም ንግድ ነክ በሆኑ ጉዳዬች ላይ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ግልፅ የሆነ አሠራር ለማዘጋጀት ታሳቢ ተደርጓ የተቀረፀ መሆኑን ገልፀዋል።
ተቋማዊ የግልግል ዳኝነት ማዕከላት የተደራጀ ያለመግባባት መፍቻ አገልግሎት በመስጠት አሰራሮችን ሙያዊ እንዲሆኑ ለማስቻል፣በዘርፉ ምርምር በማድረግና የአቅም ግንባታ ስራ ለመሥራት፣ውሳኔዎች ሙያዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣በሀገር ፍትሕ ሥርዓት እድገት ማገዝ የሚሉና ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሏቸውም ተገልፆል።
የረቂቅ ደንቡ ዋና ዓላማም ዓለም ዓቀፍ ጀረጃውን የጠበቀ ማዕከል እንዲኖር ማስቻል፣ግልፅ መስፈርቶችን መደንገግና የግልግል ዳኝነት ማዕከላት ግልፅ የቁጥጥር ሥርዓት መፍጠር መሆኑ በረቂቅ ደንቡ ተመላክቷል።
ውይይቱን የመሩትና መድረኩን ያጠቃለሉት በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አዲስ ጌትነት በበኩላቸው የግልግል ዳኝነት ማእከላትን ማቋቋም ያለ ደንብ ሙሉ እንደማይሆን በመረዳት ተሳታፊዎች በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦችን በመስጠትና ደንቡን የበለጠ በማጎልበት በፍጥነት እንዲፀድቅና ወደ ትግበራ እንዲሸጋገር ለማገዝ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከዚህ ቀደም በተደረገ የመጀመሪያ ውይይት የተሰጡ ጠቃሚ አስተያየቶችን በማካተት የተዘጋጀው ረቂቅ እጅጉን የሚበረታታ መሆኑን በማመስገን የደንቡ መዘጋጀትና መኖር አስፈላጊነት አጠያያቂ አለመሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ማእከላት መዳረሻ እንድትሆን ለማስቻል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ሲሆኑ ለዚህ ተግባር መሳካትም የፍትሕ ሚኒስትር በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት በመመስረት በበላይነት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።