ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የአርማታ ብረት በሙስና ለማውጣት የሞከሩ ሁለት ተከሳሾች ላይ ክስ ተመሰረተ

Two Defendants Charged with Aggravated Corruption for Attempting to Misappropriate Over 2 Million Birr Worth of Reinforcement Steel Belonging to the Addis Ababa Housing Development Corporation

በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ትክክለኛ ያልሆነ የበር መውጫ ወረቀት በማዘጋጀት የሚጠብቁትን ንብረት በተሽከርካሪ በማስጫን ይዘው ከግቢ ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር በዋሉት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ፕሮጀክት ጽ/ቤት ንብረት አስተዳደር ባለሙያውና ተባባሪው ላይ በፈፀሙት በሥራ ተግባር የሚፈጸም የመውሰድና መሰወር ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

ተከሳሾች ታደሰ ሽፈራው እና ሞላ ይርጋ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(ሀ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 15(1)(ለ) እና (2) ላይ የተመለከተውን በመተላለፋቸው ነው ክሱ የቀረበባቸው፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ተከሳሽ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ፕሮጀክት ሁለት ቤቶች ልማት ጽ/ቤት ንብረት አስተዳደር ባለሙያነት፣ 2ኛ ተከሳሽ ሞገስ ብርቱካን እና ጓደኞቹ የጥበቃ ኤጀንሲ ውስጥ ሽፍት መሪ ሆነው ተመድበው ሲሰሩ ተገቢ ያልሆነ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት በማሳብ 1ኛ ተከሳሽ በስራው ኃላፊነት የሚጠብቀውን ንብረትነቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ፕሮጀክት ሁለት ቤቶች ልማት ጽ/ቤት የሆነውን ባለ 10 ዲያሜትር ብዛት 2 ሺ 598 ቤርጋ የዋጋ ግምቱ 2 ሚሊዮን 376 ሺ 619 ብር የሆነ የአርማታ ብረት የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 03 አያት አርባ ዘጠኝ ተብሎ ከሚጠራው አከባቢ በኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱ ጽ/ቤት ንብረት ክፍል ውስጥ ተቀምጦ የነበረው ብረት ውስጥ 1ኛ ተከሳሽ በየካቲት 2 ቀን 2014 ተረካቢ አንዱአለም የሕንጻ ተቋራጭ ድርጅት የሚል ብዛቱ 446 ኪ.ግ የተሸከርካሪ ስም ጠቅሶ ትክክለኛ ያልሆነ የበር መውጫ ወረቀት አዘጋጅቶ 4ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር በሚያሽከረክረው ሲኖትራክ ተሽከርካሪ በማስጫን፤ 2ኛ ተከሳሽም ይህንን ብረት ሲጫን ቆሞ እየተቆጣጠር የነበረ እና ተሽከርካሪው ላይ የተጫነው የብረት መጠን የበር መውጫው ላይ ከተጻፈው የብረት መጠን ብልጫ እንዳለው እያወቀ እንዲሁም በመውጫ ላይ የተጻፈው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን እያወቀ አጃቢ በመሆን ተሽከርካሪ ውስጥ በመግባት ከግቢ ሊወጡ ሲሉ የበር መውጫ ሲጠየቁ ያቀረቡት ሰነድ ሀሰተኛ የበር መውጫ መሆኑ በመረጋገጡ በቁጥጥር ስር የዋሉ በመሆኑ ተከሳሾች በፈፀሙት በሥራ ተግባር የሚፈጸም የመውሰድና መሰወር ከባድ የሙስና ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት 1ኛ ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ ተነቦለታል፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ችሎትም 1ኛ ተከሳሽ በቀረበበት ክስ ላይ የሚያቀርበውን የክስ መቃወሚያ እና የ2ኛ ተከሳሽን መቅረብ ለመጠባበቅ ለሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Tagged Under: ababa • addis • anti-corruption proclamation • bribery • charges • corporation • Corruption • criminal • Criminal Charges • development • embezzlement • ethiopian criminal code • federal • Federal High Court • Forgery • Fraud • high • housing • illegal export • lideta district court • misappropriation • reinforcement • steel
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች