የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት እና በዓለም ዓቀፍ የፍልሰት ድርጅት ትብብር የተዘጋጀና ትኩረቱን በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን የማዘዋወርና ከሀገር የማስወጣት ወንጀሎችን በመከላከል ላይ ያደረገ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለፌዴራል እና የክልል የፍትሕ አካላት በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
ከህዳር 30- ታህሳስ 05 2017ዓ.ም ድረስ በሚሰጠው በዚህ ሥልጠና ላይ አዲስ አበባ እና ድሬደዋን ጨምሮ ከኦሮምያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተወከሉ ዐቃብያነ ሕግ፣ የወንጀል መከላከል ሀላፊዎችና የምርመራ ክፍል መሪዎች የሚሳተፉበት መሆኑ ታውቋል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳሬክቶሬት ምክትል ዳሬክተር እጣወርቅ ተስፋዬ የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክቶ እንደተናገሩት በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን የማዘዋወርና ከሀገር የማስወጣት ወንጀሎችን ለመከላከል የፌዴራል እና የክልል የፍትሕ አካላት መደበኛ በሆነ መንገድ ምርመራ እና ክስ የመመስረት ስራን በማከናወን ላይ ቢሆኑም፤ ወንጀሉ እየተፈፀመ የሚገኝበት ደረጃ ሰፊና ውስብስብ በመሆኑ ምክንያት በርካታ ዜጎች እየተጎዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መደበኛውን የክስ ሂደት ተከትሎ በመሥራት ብቻ ወንጀሉን መከላከልና ህገወጥ አዘዋዋሪዎችን የማስቀጣት ስራው የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳላስቻለ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ዳይሬክተሯ አያይዘውም ወንጀሉን ለመከላከልና አጥፊዎችንም ለማስቀጣት እየተሰራበት የሚገኘው የተወሰኑ ተበዳዮች ብቻ የሚሰጡትን ጥቆማ መሠረት ያደረገ በመሆኑ የሚከፈቱት መዝገቦች በምስክሮች ላይ እንዲወሰኑ ስላደረገው በዚህ መስክ ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ አስረድተው፤ የማዘዋወርና ከሀገር የማስወጣት ወንጀሎች ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እንዲቀጥል ማድረጉን በሌላም በኩል በሀገር ገፅታ ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ከዚህ አንፃር በመደበኛው አሠራር መቀጠሉ ውጤታማ ሊያደርገን ስለማይችል ከዚህ በኋላ የቅድመ ጥቆማ ዘዴን በመከተል ስራውን ማከናወን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
በመሆኑም በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን የማዘዋወርና ከሀገር የማስወጣት ወንጀሎችን ለመከላከል እንዲቻል የፍትሕ አካላት ውጤታማ የሆነ ስራን እንዲያከናውኑ ለማገዝ ታስቦ የተዘጋጀውና ለ6 ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ሥልጠና ላይ ስለፍልሰት ምንነትና ምክንያቶቹ፣ በሀገር እና ዓለም ዓቀፍ ደረጃ ስላለው ህገወጥ ፍልሰትና ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ስለሚፈፀሙ ወንጀሎችና ጉዳቶች፣ በኢትዮጵያ የህገወጥ ፍልሰት መተላለፊያ አካባቢዎች እና ተያያዥ ስለሆኑ ጉዳዮች ተነስቶ ግንዛቤ የሚሰጥ ሲሆን፤ ሰልጣኞች በበኩላቸው ያላቸውን ተሞክሮ እያነሱ እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡