ሐሰተኛ የአሜሪካን ዶላር ሲሸጡ የተገኙት ጥላሁን ሙሉጌታ እና ሐጎስ ግርማይ በእስራት እንዲቀጡ ተደረገ

Tilahun Mulugeta and Hagos Girmay Sentenced to Imprisonment for Selling Counterfeit US Dollars

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ 19 ሺ 200 የአሜሪካን ዶላር ሐሰተኛ ገንዘብ እውነተኛ እንደሆነ አስመስለው እንዲዘዋወር ለማድረግ በማሰብና በኢትዮጵያ ብር ሊቀያየሩ በመነጋገር ይዘው በተገኙ ሁለት ግለሰቦች ላይ ክስ መስርቶ በ8 ዓመት ከ5 ወር እስራት እንዲቀጡ አድርጓል፡፡

ክርክሩን የመራው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 11ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ነው።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ጥላሁን ሙሉጌታ እና ሐጎስ ግርማይ የተባሉት ተከሳሾች ሐሰተኛ ገንዘብ እውነተኛ እንደሆነ አስመስለው ሚያዝያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ዲአፍሪክ ሆቴል አካባቢ አንዱን የአሜሪካ ዶላር በ62 የኢትዮጵያ ብር ሊቀያየሩ በስልክ ከተስማሙ በኋላ 2ኛ ተከሳሽ ሀሰተኛ የአሜሪካን ዶላር ባለ100 ኖት ብዛቱ 97 የሆነ እንዲሁም በዶላሩ ልክ የተቆረጠ ወረቀት ብዛቱ 95 ጋር በማቀላቀል በአጠቃላይ 19 ሺ 200 የአሜሪካን ዶላር በ62 ብር ሲመነዘር 1 ሚሊዮን 190 ሺ 400 ብር የሚያወጣ ዋጋ እንዳለው በማስመሰል ከ1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ጋር ለመቀያየር ሲሉ የተያዙ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ሀሰተኛ ገንዘብ ይዞ መገኘት ወይም ማቅረብ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም ያሉ ሲሆን ዐቃቤ ሕግም የሰው፣ የሰነድ እና ኤግዚቢት ማስረጃዎችን አቅርቦ በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን መሠረት ተከሳሾች 3 የመከላከያ ማስረጃ አቅርበው የተከራከሩ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ ያላስተባበሉ በመሆኑ ተከሳሾች ይከላከሉ በተባለበት ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ናችሁ ብሏቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም በቅጣት አወሳሰን መመሪያ 02/2006 መሠረት የወንጀል ደረጃውን 9 ላይ በማሳረፍ በእርከን 31 ስር መነሻ ቅጣት በመያዝ፣ ወንጀሉ በስምምነት የተፈፀመ በመሆኑ የቅጣት 1 ማክበጃ በመያዝ፣ እንዲሁም ሁለቱም ተከሳሾች ሪከርድ የሌለባቸው በመሆኑ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው፣ ቦንድ ገዝተው ለሀገር አስተዋፅኦ ያደረጉ በመሆናቸው፣ ህመምተኛ በመሆናቸውና እድሜያቸው የገፋ በመሆኑ በጥቅሉ 5 የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው በእርከን 27 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን እያንዳንዳቸው በ8 ዓመት ከ5 ወር እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡

Tagged Under: counterfeit_us_dollars • currency_counterfeiting • economic_crime • federal_high_court • financial_crime • Fraud • imprisonment • Judgment • lideta_district • sentence
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች