መንግስት ከቀረጥና ታክስ ላይ ከ1 ሚሊየን 800ሺ ብር በላይ እንዲያጣ አድርገዋል በተባሉ ሶስት ግለሰቦች ላይ ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶ ከ11 እስከ15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ አደረገ

Three Individuals Sentenced to 11 to 15 Years Imprisonment for Causing Over 1.8 Million Birr Loss to Government in Customs and Tax Evasion

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ ጋር በመሆን መንግሥት ከቀረጥና ታክስ ላይ ከ1 ሚሊየን 800 ሺ ብር በላይ እንዲያጣ አድርገዋል በተባሉ ሶስት ግለሰቦች ላይ ምርመራ በማጣራት ክስ መስርቶ ከ11 እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ማድረግ ችሏል፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አቶ አዲሱ ታየ፣ አቶ ተመስገን በዛብህ፣ አቶ ጌታ መሳይ ከተማ የተባሉት ተከሳሾች በመንግሥት የገንዘብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ 1ኛ ተከሳሽ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድ ባለሥልጣን የዳታ ኢንኮደር ባለሙያ በመሆን በመሥራት ላይ እያለ 2ተኛ ተከሳሽ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት በቱሪስት ቪዛ ወደ ሀገር ውስጥ በአንድ ግለሰብ ስም በጊዚያዊነት የገባውን ራቫ ፎር መኪና መሳይ ከተማ ለተባለው ተከሳሽ ውክልና እንደተሰጠው በማስመሰልና ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት በሌላ የተሽከርካሪ አስመጭ በሆኑ ግለሰብ ስም ቀረጥና ታክስ ተከፍሎ ወደ ሀገር ገብቷል የሚል ሀሰተኛ ዲክለራሲዮን፣ እና መንግስታዊ የሆኑ ሀሰተኛ ሰነዶችን ይዞ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ቀርቧል፡፡

በዚህን ጊዜ 1ኛ ተከሳሽ ተሸርካሪው ምንም አይነት ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለበት መሆኑን እያወቀ ባለው የስራ ኃላፊነት በመጠቀም በጉሙሩክ የመረጃ ቋት ላይ ያልተመዘገበና ሀሰተኛ የሆነ የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን የተሽከርካሪ ማረጋገጫ ሪፖርት ቅጽ በማዘጋጀት ተሽርካሪው 6 መቶ 30ሺ 476 ብር ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበታል በማለት በኃላፊነት የተሰጠውን ክብ ማህተም በሀሰተኛ ቅጽ ላይ በመምታት እና በመፈረም ለሁለተኛ ተከሳሽ ይሰጠዋል፤ በሌላ በኩል ሁለተኛ ተከሳሽም የተሰጡትን ሀሰተኛ ሰነዶች ተጠቅሞ የተሽከርካሪውን የባለቤትነት ማረጋገጫ ሊብሬ በአራተኛ ተከሳሽ ስም በመውሰድ ሌላ ሶስተኛ ተከሳሽ መኪናው የእህቴ ነው በማለት መኪናውን ሽጦ ገንዘቡን ለመቀበል ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል፤ አራተኛ ተከሳሽ ከሁለተኛና ሶስተኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር በስሙ ታርጋና ሊቭሬ ማውጣት እንዲችል ሀሰተኛ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ለሁለተኛ ተከሳሽ በመስጠት በስሙ ታርጋና ሊብሬ እንዲወጣ አድርጓል፡፡

በዚህም ምክንያት ዐቃቤ ሕግ ሶስቱ ተከሳሾች መንግሥት ከቀረጥና ታክስ ሊያገኝ ይገባ የነበረውን ከ1ሚሊዮን 800ሺ ብር በላይ እንዲያጣ ያደረጉ በመሆኑ ሆን ብለው በፈጸሙት ሥልጣንን ያለ አግባብ መገልገል ወንጀል እና የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኝት እና በመንግሥት ላይ ጉዳት ለማድረስ ሆን ብለው በፈጸሙት የሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል ሁለት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ሁለተኛ ተከሳሽ በፈጸመው በተጭበረበሩ ወይም ህገ-ወጥ የሆኑ ደረሰኝ መጠቀም ወንጀል በ3 ተኛ ክስ ተከሷል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተውም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 5ተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት በ1ኛ ተከሳሽ ላይ 15 ዓመት በ2ተኛ ተከሳሽ ላይ በ14 ዓመት እንዲሁም በ4ተኛ ተከሳሽ ላይ በ11 ዓመት ጽኑ እስራትና በእያንዳንዳቸው ላይ የ20 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡

Tagged Under: bribery • conspiracy • Crime • Criminal Charges • customs • customs declaration • customs fraud • Documents • Economic • Economic Crime • evasion • federal • Federal High Court • Forgery • Fraud • fraudulent • fraudulent documents • Government • government revenue loss • imprisonment • lideta district court • loss • misuse of authority • Revenue • sentence • Tax • Tax Evasion • vehicle registration
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች