በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ከተለያዩ ተቋማት ለሚቀርቡ የሕግ ምክር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እና የሕግ ማርቀቅ ስራ ይገኝበታል፡፡ ዳይሬክቶሬቱ በ2ዐ15 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 41 ጉዳዮች ላይ የማማከር፣ አራት ህጎችን የማርቀቅ እና ለሌሎች የመንግሥት ተቋማትም በሕግ ማርቀቅ ስራ ላይ ድጋፍ ማድረጉን የዳይሬክቶሬቱ ም/ዳይሬክተር ጀኔራል የሆኑት ወ/ሪት ቃልኪዳን ደረጀ ገልጸዋል፡፡
እንደ ምክትል ዳይሬክተሯ ገለፃ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከልዩ ልዩ አካላት የሚቀርቡ የሕግ ምክር ጥያቄዎችን ሀገሪቷ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ከህገ መንግስቱ፣ ከፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና ከሌሎች ህጎች አንጻር በመመርመር የሕግ ምክር እንዲሰጥባቸው በቀረቡ 41 ጉዳዮች ላይ በጽሑፍ፣ በመድረክ በመገኘት፣ ፊትለፊት በመገናኘት እና በመሳሰሉት ዘዴዎች የሕግ ምክር ተሰጥቷል።
ዳይሬክቶሬት ጀኔራሉ በስድስት ወራት ውስጥ አራት ህጎችን የማርቀቅ ስራ ያከናወነ ሲሆን የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የማዕድን ሚኒስቴር እያዘጋጅዋቸው በሚገኙ ህጎች የማርቀቅ ስራ ላይ በመሳተፍ አስፈላጊው ድጋፍ የተደረገ መሆኑን ወ/ሪት ቃልኪዳን አክለው ገልጸዋል፡፡