የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶችን እውቅና ለመስጠት እና ሥራ ለማስጀመር ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም፣ በባህርዳር ከተማ ባካሄደው መድረክ ላይ ለክልሉ ማኀበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ማቋቋሚያ የሚውል ድጋፍ አድርጓል፡፡
በመድረኩ የፍትሕ መኒስቴር የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃን ተገኝተው፣ ከወርልድ ቪዥን በተገኘ ድጋፍ በክልሉ ለሦስት የማኀበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ማቋቋሚያ የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስረክበዋል።
ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት የዘመናዊ ፍትሕ ሥርዓትን ሳይተካ፣ ፍትሕን ወደ ሕዝብ የሚያደርስና ማህበራዊ ሰላምን በማጠናከር የሚያግዝ ጠንካራ ባህላዊ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የመንግሥትና የልማት አጋሮች ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ለማኀበረሰቡ ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ ጉልህ ሚና ባለው የመሠረተ ማኀበረሰብ የፍትሕ አገልግሎት ማዕከላት በክልሉ ለማስፋፋት ሌሎች አጋሮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ በማቅረብ ወርልድ ቪዥን ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ፍትሕ ሚኒስቴር ወደፊትም ተመሳሳይ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አክለው ገልጸዋል።