በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ የስራ ክፍያ በአፋጣኝ እንዲከፈል አደርጋለው በማለት ከኮንስትራክሽን እቃ አቅራቢ ድርጅቶች ላይ በራሱና በባለቤቱ ስም 344 ሺ ብር ጉቦ በመቀበል ለግል ጥቅሙ ባዋለው በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግዥና አቅርቦት ንብረት አስተዳደር ቡድን መሪ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተበት፡፡
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ኤልያስ መሐመድ የተባለው ተከሳሽ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በልዩ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ መምሪያ ስር በሚገኘው የኮዬ ፈጬ ሁለት ሎት 2 እና 3 መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግዥና አቅርቦት ንብረት አስተዳደር ቡድን መሪ ሆኖ ሲሰራ፣ በሥራው ግዴታ ማድረግ የማይገባውን ለማድረግ በማሰብ አንድ ግለሰብ በውክልና የሚያስተዳድራቸው ደጅይጥኑ አለነ ማሽነሪ ኪራይና ትራንስፖርት አገልግሎት እና ብርሃኑ አሰፋ የኮንስትራክሽን ማቴሪያል አቅራቢ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተለያየ ጊዜ ባወጣው የተሽከርካሪና ማሽነሪ ኪራይ እንዲሁም የግንባታ እቃ አቅራቢነት ጨረታ ላይ ተሳትፈው አሸናፊ በመሆናቸው ደጅይጥኑ አለነ ማሽነሪ ኪራይና ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በ2014 ዓ.ም በተለያዩ ቀናት በተፈጸመው የሎደርና ሮሎ ማሽነሪዎች ክራይ ውል፣ የገልባጭ ተሽከርካሪ ኪራይ ውል፣ እና የውሃ ቦቴ ተሽከርካሪ ክራይ ውል እንዲሁም ብርሃኑ አሰፋ የኮንስትራክሽን ማቴሪያል አቅራቢ ድርጅት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋርም በ2013 ዓ.ም በተፈፀመው ክረሽድ ቤዝ ኮርስ ማቴሪያል አቅራቢነት ውል መሠረት ለተሰሩ ስራዎች ክፍያ እንዲፈፀምለት ጥያቄ ሲያቀርብ ተከሳሹ ክፍያ በአፋጣኝ እንዲከፈልህ አደርጋለው እንዲሁም ተጨማሪ ስራ እንድታገኝ አደርጋለው ገንዘብ ስጥኝ በማለት ከመስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ሰኔ 02 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ፡-
በተበዳይ ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ወደ ተከሳሽ የባንክ ሂሳብ ቁጥር በተለያዩ ቀናት በሞባይል ባንኪንግ 3 መቶ 20 ሺ ብር እንዲተላለፍ በማድረግ ገንዘቡን ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅሙ ያዋለ እና እንዲሁም በተበዳይ ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ወደ ተከሳሽ ባለቤት የባንክ ሂሳብ ቁጥር በተለያዩ ቀናት በሞባይል ባንኪንግ 24 ሺ ብር እንዲተላለፍላት በማድረግ፤ በአጠቃላይ ተከሳሹ በራሱ እና በባለቤቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ከግል ተበዳይ ሂሳብ ቁጥር በሞባይል ባንኪንግ 344 ሺ ብር እንዲያስተላለፍለት በማድረግ ጉቦ የተቀበለ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ችሎትም ተከሳሽ ክሱ ተነቦለት የክስ መቃወሚያ ካለ ለመጠባበቅ ለጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ይህ ዘገባ የቀረበው ዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱን ለመግለጽ ሲሆን ተከሳሽ ከፍርድ በፊት እንደንጹህ የመቆጠር መብት አለው።