የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ 634 ሺ 345 ብር ቀረጥና ታክስ የሚከፈልባቸው የመኪና መለዋወጫዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገባን ዕቃ ማጓጓዝ የኮንትሮባንድ ወንጀል ፈፅመዋል ባላቸው ተከሳሾች ላይ ክሱን አሰማ፡፡
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚስረዳው 1ኛ ተከሳሽ ተንሰው ተረፈ፣ 2ኛ ተከሳሽ ተሲሳ አስያ የተባሉ ተከሳሾች ተገቢው የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት ሳይፈፀምባቸው ወደ አገር ውስጥ የገቡ መሆናቸውን ማወቅ ሲገባቸው ጠቅላላ ዋጋቸው 13 ሚሊዮን 414 ሺ ብር የሚያወጡ ቀረጥና ታክስ 634 ሺ 345 ብር የሚከፈልባቸው ብዛታቸው 3 ሺ 946 ብር የመኪና መለዋወጫዎችን ኤፍ ኤስ አር መኪና ላይ በተሰራ ሻግ ውስጥ ጭነው 1ኛ ተከሳሽ መኪናውን እያሽከረከረ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የ1ኛ ተከሳሽ ረዳት ሆኖ እየሰራ ከአዳማ ከተማ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አቅጣጫ ሲያጓጉዙ ቱሉዲምቱ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ኬላ ላይ ስለተያዙ በፈፀሙት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገባን ዕቃ ማጓጓዝ የኮንትሮባንድ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ክሱ የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾች ቀርበው የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም በማለት ክደው የተከራከሩ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ያሰባሰበውን ማስረጃ እንዲያቀርብ ለታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡