በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱም የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ አጭር ማብራሪያ አቅርበዋል።
በዚህ ጊዜ ክብርት ሚኒስትሯ የረቂቅ አዋጁ ዋና ዓላማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል እና በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ማስመለስ መሆኑን ገልጸዉ መንግሥት የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ለመከላከል ካለው ቁርጠኝነት እንዲሁም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም ዓቀፍ ህጎች ለአዋጁ መውጣት ምክንያት መሆናቸውን አክለዋል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ያሉት ህጎች ውስንና የተበታተኑ መሆናቸውን አንስተው፤ የሀብት ማስመለስን በሚመለከት ሁሉን አቀፍና አንድ ወጥ የሆነ ሕግ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል ።
አዋጁ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረት የሚመለስበትን ስነ-ስርዐታዊ ጉዳዮችን እና ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ጋር ተያይዞ ፍትሀብሔራዊ ተጠያቂነትን የሚመሰርት መሆኑን ክብርት ሚንስትሯ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የውይይቱ ተሳታፊዎችም ቢስተካከሉ እና ቢካተቱ ያሏቸውን ሀሳብና አስተያየቶች አቅርበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ መድረኩ ጥሩ ግብአት የተገኘበት መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም የተነሱ ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ የውሳኔ ሃሳብ የሚዘጋጅ እንደሆነ ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው አዋጁ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል እንዲሆን በተነሱ አስተያየቶች መሠረት ከሌሎች ህጎች ጋር እንዳይጋጭ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል ።
የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በመድረኩ ለተነሱ አስተያየት እና ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
በውይይቱ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከፍርድ ቤቶች፣ ከጠበቆች ማህበር፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከንግድ ባንክ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ፣ ከኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተልጀንስ እና ከሌሎችም ተቋማት የመጡ የስራ ሃላፊዎች መገኘታቸዉን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።