በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ጋር በጋራ ያከናወነውን ምርመራ መሠረት አድርጎ 1ኛሲፈን አበራ፣ 2ኛ ሀዊ ደሮ፣ 3ኛ ይርገድ ሙሉጌታ፣ 4ኛ ሀብታሙ አበራ፣ 5ኛመለሰ አብጤ፣ 6ኛ ቢኒያም ወንድወሰን፣ 7ኛ በሀይሉ አባተ፣ 8ኛኦሊያ በቀለ እና 9ኛ አሳምነው ተስፋዬ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ የመሰረተ ሲሆን 3ቱ የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳር ባለሙያዎችን ጨምሮ 9 ግለሰቦች ላይ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀትና በመመሳጠር በአርሶ አደር ስም የባለይዞታነት መብት በመፍጠርና ይህንኑ ይዞታ ለ3ኛ ወገን ህገ ወጥ በሆነ ሽያጭ በማስተላለፍ ከ24 ሚሊየን ብር በላይ ጥቅም አካብተዋል በማለት በከባድ የሙስና ወንጀል 4 ተደራራቢ ክሶችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ የሙስና ወንጀል ችሎት መስርቶ ክርክሩን እያካሄደ ይገኛል፡፡
የተከሳሾችን የዋስትና መብት በተመለከተ የተከሰሱበት የወንጀል ድንጋጌ የዋስትና መብትን የሚያስከለክል በመሆኑ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ ይገኛሉ።
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾች በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አቶ ደበሌ ያደታ የተባሉ ነባር አርሶ አደርና እና ወራሾቻቸው ግብር እየከፈሉና እያስተዳደሩት የቆዩትን አጠቃላይ ስፋቱ 638 ካሬ ሜትር የሚሸፍነውን መሬት የይዞታ መብት እንዲፈጠርላቸው ጥያቄ አቅርበው ጉዳዩ በሂደት ላይ እያለ ከ5ኛእስከ7ኛ ያሉ ተከሳሾች የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ይዞታ አስተዳር ጽ/ቤት ሰራተኞች ሆነው ሲሰሩ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ግለሰቦቹ ሊያገኙት የሚችሉትን ህጋዊ ጥቅም ወይም የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ለ1ኛ እና ለ8ኛ ተከሳሾች ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ አሳልፈው ለመስጠት ይመሳጠራሉ፡፡
በዚህም ሂደት ከ1 እስከ 4 ያሉ ተከሳሾች በአካባቢው በአርሶ-አደርነት ወይም በአርሶ-አደር ልጅነት የማይታወቁ፣ በይዞታዎቹ ላይ የማይኖሩ እና የማያስተዳድሩ ሆነው እያለ አርሶ-አደር እንደሆኑ የሚገልጹ በሐሰት የተዘጋጁ ሰነዶችን በመገልገል፣ በይዞታዎቹ ላይ ቤት ሰርተው እየኖሩ እና እያስተዳደሩት እንደሆነ በማስመሰል፣ ያለአግባብ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች በህገ-ወጥ መንገድ በመውሰድ ውስን የሆነው የሕዝብ ሀብት በፍትሀዊነት ጥቅም ላይ እንዳይውልና የመሬት ወረራ እንዲፈጸም ያደረጉ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆንና በልዩ ተካፋይነት በፈፀሙት ሥልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾች ክሱ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም ጥፋተኞችም አይደለንም ሲሉ ክደው በመከራከራቸው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ የወንጀሉን መፈጸም የያስረዱ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለችሎቱ በማሰማት ላይ ይገኛል፡፡
ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ሕግ ቁጥር 32(1) (ሀ) (ለ) ፣33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1)(ሀ(2)፣ 23 (2) እና (3) በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትና ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29(1) (ሀ) እና (ለ) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ እንዲሁም የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 123(1) (ለ) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በ4 የተለያዩ ወንጀሎች ነው ክስ የቀረበባቸው።
ተከታዮቻችን የክርክር ሂደቱን ተከታትለን የምንዘግብ ሲሆን የዘገባው ዓላማ የክርክር ሂደቱን ማሳየት ሲሆን ተከሳሾች ከፍርድ በፊት እንደ ንጹህ የመገመት ህገመንግታዊ መርህ እንደተጠበቀ ነው ፡፡